ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጠመው

ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ የሚያካሂደውን የአዲስአበባ እና የአካባቢ ምርጫ አስመልክቶ ያዘጋጀውን
ጊዜያዊ የምርጫ ማስፈጸሚያ ጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመምከር ባለፈው ሐሙስ ዕለት በአዳማ የጠራው ስብሰባ ከተቃዋሚ
ፓርቲዎች ያልተጠበቀ ተቃውሞን በመቀስቀሱ ሁኔታው የቦርዱን አመራሮች አደናግጦ እንደነበር አንዳንድ የስብሰባው
ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

ቦርዱ በጠራው በዚሁ ስብሰባ ላይ ከ70 በላይ ፓርቲዎች ተወካዮቻቸውን የላኩ ሲሆን ስብሰባው በተጠራበት ጉዳይ
ማለትም በቀጣዩ ምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ መወያየት ከተጀመረ በኃላ ብዙዎቹ ፓርቲዎች በስብሰባው አካሄድ ላይ ጥያቄ
አንስተዋል፡፡

በዕለቱ ስብሰባ ላይ የተገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባልተለመደ ሁኔታ በጋራ ድምጻቸውን ያሰሙበት ጉዳይ
ስለምርጫው ከመነጋገራችን አስቀድሞ የመጫወቻው ሜዳ ለሁሉም እኩል መሆን አለበት፣በዚህ ጉዳይ ላይ ቦርዱ ከገዥው ፓርቲ ጋር እንድንወያይ ሁኔታዎችን ካላመቻቸ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄዱ ፋይዳ የለውም በሚለው አቋማቸው  ነው፡፡  ይህ የፓርቲዎች ጠንካራ አቋም ከተሰማ በኃላ በተነሳው ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዜ መድረክ እንደሚያመቻቹ የቦርዱ ስብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ቃል በመግባት ነገሩን ለማርገብ ሞክረዋል፡፡

ቀጥሎም እያንዳንዱ ፓርቲ ለደቂቃዎች እንዲናገር፣በንግግሩም አሉ የሚባሉ ችግሮችን እንዲጠቁም ተብሎ ሁሉም መናገራቸውን የዜና ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር   “የቦርዱ ኃላፊዎች ስለቀጣዩ ምርጫ ሲያወሩ ያለፉት ምርጫዎች
እንከን የለሸ እንደነበሩ አስመስለው ነው፡፡በተጨባጭ ግን የፖለቲካ ምህዳሩ በመጥበቡ በአፈናና በማጭበርበር ገዥው
ፓርቲ ያለምንም ሃፍረት 99.6 በመቶ የሚያሸንፍበት የምርጫ ድራማ እያየን በመሆኑ ይህ ችግር ሳይፈታ ምርጫ
መሳተፉ ሕገወጥነትን በማጀብ ሕጋዊ ከማስመሰል ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም” ብለዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙት የመድረክ ተወካዮች ቦርዱ ስለምርጫ ሒደት ከማውራቱ በፊት ባሉት ችግሮች ላይ አገራዊ
ውይይት እንዲካሄድ በዕለቱ ስብሰባ ከተገኙ አባላት ከግማሽ በላይ የድጋፍ ፊርማ አሰባስበዋል፡፡

በወጣው ጊዜያዊ የምርጫ አፈጻጸም ጊዜ ሰሌዳ መሰረት የአዲስአበባ እና አካባቢ ምርጫ ሚያዚያ 6 ቀን፣ የአዲስአበባ
የወረዳ ም/ቤት እና የደቡብ ክልል የቀበሌ ም/ቤት አባላት ምርጫ ሚያዝያ 16 ቀን 2005 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
ቦርዱ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ የሌሎች የተጓደሉ አባላት ምርጫ ከዚህኛው ምርጫ ጋር አዳብሎ ስለማካሄዱ የታወቀ ነገር የለም፡፡

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን በተለይም በክልሎች ሞት፣ስደት፣እስራት፣ከስራ መፈናቀል፣ቤተሰብ
መበተንን፣ከሃብትና ንብረት መፈናቀልን የሚያስከትል ሲሆን ፓርቲዎቹም ጽ/ቤታቸውን በማሸግ፣ስብሰባ እንዳይካሄዱ
በማወክ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከመችውም ጊዜ በበለጠ ጠንክሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ፓርቲዎቹ በየጊዜው
ከሚያቀርቡት አቤቱታ መረዳት ይቻላል፡፡