ሜጄር ጄኔራል ገብሬ አድሃና በአብዬ ግዛት ተሾሙ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2010) ሜጄር ጄኔራል ገብሬ አድሃና በአብዬ ግዛት የሰላም አስከባሪው አዛዥ ሆነው በተባበሩት መንግስታት መሾማቸው ተገለጸ።

የሕወሃቱ ታጋይ ጄኔራል ገብሬ አድሃና የሚተኩት ሌላውን የሕወሃት ታጋይ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ግደይን እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።

የዚህ ተልዕኮ ምክትል አዛዥ ሆነው ተሹመው በመስራት ላይ የሚገኙትም ሌላዋ የሕወሃት ታጋይ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ኪሮስ ናቸው ።

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡበት አቢዬ ግዛት ከተሰማራው 4ሺ ያህል ሰላም አስከባሪ 3ሺ 900 የሚሆኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች በመሆናቸው የአዛዥነቱ ስፍራ በቋሚነት ለኢትዮጵያ የተለቀቀ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

ሆኖም ለኢትዮጵያ የተለቀቀው የአዛዥነት ስፍራ በህወሃት ታጋዮች ቁጥጥር ስር ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትላንት ለአቢዬ ግዛት የሰላም አስከባሪ አዛዥነት የሾሟቸው ሜጄር ጄኔራል ገብሬ አድሃና ወልደዝጊ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ በኢትዮጵያ የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው ሲልም መግለጫው ያመለክታል።

የሕወሃቱ ታጋይ ጄኔራል ገብሬ አድሃና በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ 38 አመታት እንዳገለግሉም ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት አባል የሆኑት ግን ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት በአብዬ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ አዛዥ በመሆን በማገልገል ላይ ያሉት ሌላው የሕወሃት ታጋይ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ግደይ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሚያዚያ 23/2018 ጀምሮ ሃላፊነቱን ለአዲሱ ተሿሚ ያስረክባሉ።

የዚህ ተልዕኮ ምክትል አዛዥ በመሆን የሚያገለግሉትና አሁንም በዚሁ ሃላፊነት ላይ የቀጠሉት እንስቷ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ኪሮስም የህወሃት ታጋይ ናቸው።

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡበት አቢዬ ግዛት የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ሃይል ብዛት 4ሺ ያህል ነው።

ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 3 ሺ 900 ያህሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ናቸው።

በአጠቃላይ በተለዕኮው 29 ሀገራት ቢሳተፉም ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ተብሎ የሚጠቀሰው ናይጄሪያ ያሰማራቻቸው 3 ወታደሮች ብቻ ናቸው።

በመሆኑም ለዚህ ተልዕኮ በቋሚነት አዛዥነቱ የሚሰጠው ለኢትዮጵያ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ስፍራው ለሕወሃት ታጋዮች እንዲሰጥ በተከታታይ የሕወሃት ታጋዮችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

የብአዴን ታጋይ የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ኢብራሒም ሙሳና የኦሕዴድ ታጋይ የነበሩት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በመሃለ እንዲገቡ ከተደረገበት አጋጣሚ በቀር ሁሉም አዛዦች የሕወሃት ታጋዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የተሰማሩባቸው ሌሎች ተልዕኮዎች በሱዳን ዳርፉርና የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ሲሆን በእነዚህ ተልዕኮዎች የአዛዥነቱ ስፍራ የሚሰጠው ለሌሎች ሃገራት እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ማወጇን ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ በደቡብ ሱዳን በተሰማራው የሰላም አስከባሪ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ተሳትፎ በ1ሺ 494 ወታደሮች እንደሆነም ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን በአጠቃላይ የተሰማራው ሃይል 12ሺ 523 መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

7 አመታትን ባስቆጠረው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የአዛዥነቱን ስፍራ ኢትዮጵያ ያገኘችው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ የተሰጠው እድል በሕወሃቱ ታጋይ ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል ከ2014 እስከ 2016 ተሸፍኗል።

በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ብዛት 12ሺ 523 ሲሆን በአሁኑ ወቅት የዚህ ሃይል አዛዥ የሩዋንዳው ተወላጅ ሌተናል ጄኔራል ፍራንክ ሙሻያዩ ካማንዚ ናቸው ።

ኢትዮጵያ 2ሺ 456 ሰራዊት በመላክ በሰላም አስከባሪነት ያሰማራችበት ሌላው ተልዕኮ ዳርፉር ሲሆን ይህ ተልዕኮ በአጠቃላይ 26ሺ ሰላም አስከባሪ የተሰማራበት እንደሆነ መረዳት ተችሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥቅምት 2007 በጀመረው በዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያ 2ሺ 549 ወታደሮች፣16 ኤክስፐርቶችና 26 ፖሊሶች አሰማርታለች።

ይሁንና 11 አመታት በቆየው በዚህ የሰላም ማስከበር ሒደት ኢትዮጵያ የአዛዥነቱን ስፍራ ማግኘት አልቻለችም።

የናይጄሪያ፣ሩዋንዳ፣ታንዛኒያ፣ኬንያ፣ ፓኪስታን፣ደቡብ አፍሪካና ሴኔጋል ወታደራዊ አዛዦች በዙር በዳርፉር የሚገኘውን 26ሺ የሰላም አስከባሪ ሃይል ሲመሩ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የባንግላዴሽ ተወላጅ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ሞሐመድ ማስክደር ራህማን የዳርፉር ሰላም አስከባሪ ሃይል አዛዥ ናቸው።