ሜቴክ ገንዘብ የከለከለው ድርጅት የኦሞ ኩራዝ ፋብሪካ ስራውን ትቶ አዲስ አበባ ገባ

ጳጉ ( አንድ) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ስር በሚገነባው የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ድርሻ ወስዶ የግንባታ ስራ ሲሰራ የነበረው ፒጂኤ የተባለው የንግድ ድርጅት ለስራው ስራ መከፈል የነበረበት 40 ሚሊዮን ብር ሊከፈለው አለመቻሉን ተከትሎ አካባቢውን ለቆ ወጥቷል።

ሜቴክ መክፈል የነበረበትን ገንዘብ ለፒጄኤ ለመክፈል ባለመቻሉ፣ የድርጅቱ ሰራተኞች ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ድርጅቱ ለአንድ አመት ያክል በራሱ ወጪ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልችልም በማለት ባለፈው ሳምንት የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት ሌሊት ላይ አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል። የሜቴክ ሃላፊ ኮሎኔል ዮሃንስ ለጅንካ የጸጥታ ክፍል ስልክ በመደወል ሰዎቹ እንዲያዙ ትእዛዝ የሰጡ ቢሆንም፣ ሰዎቹ ትእዛዙ ከመሰጠቱ በፊት ጂንካን በማለፋቸው ያለችግር አዲስ አበባ ገብተዋል።

ሜቴክ የኦሞ ስኳርና ሌሎችንም ፐሮጀክቶች በበላይነት እየተቆጣጠረ ሲሆን፣ ኮንትራት ለሰጣቸው ድርጅቶች ከፍያ በወቅቱ አይፈጽምም። ድርጀቱ በአገሪቱ የሚታየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስራዬን በአግባቡ እንዳላከናውን እንቅፋት ፈጥሮብኛል የሚል ምክንያት ይሰጣል።