ሰኔ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የያዩ የቡና ጫካ በእንግሊዝኛ ስያሜው Yayu Coffee Forest Biosphere Reserve በዩኒስኮ ከተመዘገቡት ሁለት የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጫካዎች አንዱ ቢሆንም፣ የመከላከያ ብረታብረት ኮርፖሬሽን ምህንድስና ( ሜቴክ) በሚገነባው የያዩ ድንጋይ ከሰል ልማትና ማዳበሪያ ፋብሪካ ኮፕሌክስ የተነሳ ጨካው የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነበት ከማእድን ሚኒስቴር ለኢሳት የተላኩት ሰነዶች አመልክተዋል። ሜቴክ ግንባታውን የጀመረው ከማእድን ሚኒስቴር ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮምያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ፈቃድ ውጭ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች የማይገኙ የ አረቢካ የቡና ዘርና እና ሌሎችም እጽዋቶች ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ጉዳዩ ያሳሰባቸው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ ድርጊቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ያዩ ድንጋይ ከሰል ልማትና ማዳበሪያ ፋብሪካ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት በብረታብረት ምህንድስና ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ባለቤትነት ስራው በ2003 ዓም የተጀመረ ቢሆንም፣ ሜቴክ በተፈለገው ሰአት ስራውን ለማከናወን ባለመቻሉ ባለቤትነቱ ለኬሚካል ኮርፖሬሽን እንዲሰጥ ተደርጎ ሜቴክ በተቋራጭነት እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሊጂ ፋኩልቲ ኬሚካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ደግሞ በአማካሪነት እንዲሰሩት መደረጉን ሰነዶች ያመለክታሉ። ከአዲስ አበባ በ550 ኪ.ሜ፣ ከመቱ ደግሞ በ60 ኪሜ ርቀት ላይ በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት በኢሉአባቦራ ዞን ያዩ ወረዳ ዊጠቴ አካባቢ በመተግበር ላይ ያለው ፕሮጅክት፣ ከሚሴ፣ ዋጤቴ፣ አጨቦ እና ጀማቴ የተባሉ 4 አጎራባች ቀበሌዎችን ይነካል።
ፕሮጀክቱ የድንጋይ ከሰል ልማት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግንባታዎችን የሚያከናውን ሲሆን፣ በ2007 ዓም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ይሁን እንጅ ሜቴክ በተለያዩ ችግሮች መተብተቡን ተከትሎ ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ማድረስ ቀርቶ ግማሽ የሚሆነውን እንኳን መስራት ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ አሁንም ገና በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፣ ሜቴክ ስራውን ለመስራት ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጠይቆ አብዛኛውን መውሰዱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሜቴክ ግንባታውን ከመጀመሩ በፊት የማእድን ሚኒስቴር ለአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም ለኦሮምያ ክልል አካባቢ ልማት ቢሮ በቀን 05/ 01/2003 ዓም በቁጥር 229/2 በጻፈው ደብዳቤ ፣ ፕሮጀክቱ በያዩ ደን ላይ የሚኖረውን ተጽኖ እንዲገልጽ ጠይቋል። የኦሮምያ የአካባቢ ጥበቃ ልማት በ25-02-2003 ዓም በጻፈው መልስ “ የኮል ፎስፌት ማዳበሪያ ኮፕሌክስ ፕሮጀክት ሊተገበርበት የታሰበበበት ቦታ ሙሉ በሙሉ በቅርቡ Biosphere Reserve ተብሎ በዩኒስኮ እውቅና ባገኘው የደን ቦታ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የያዩ Coffee Forest Biosphere Reserve ከየትኛውም አካባቢ የጫካ ቡና ( Wild Arabica Coffee ) በብዛት በውስጡ የያዘ በብዝሃ ህይወት ( Biodiversity) የበለጸገ ነው። ስለዚህ የደን ቦታውን ከአላማው ውጭ ማዋል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ Biosphere Reserve የተቋቋመበትን ቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያለንን ስጋት ለመግልጽ እንወዳለን” የሚል መልስ ሰጥቷል።
የማእድን ሚኒስቴር እንደገና ያዩ ደን አለማቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ላስደረገው Environment and Coffee Forest Forum የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን፣ ድርጅቱን በ29/11/2010 በእንግሊዝኛ በጻፈው የመልስ ደብዳቤ The proposed mining areas and plants fall in the buffer zone and transition areas of the Yayu Coffee Forest biosphere Reserve. The Yayu Coffee Forest Biosphere Reserve is one of the first ever two biosphere reserves registered by UNESCO in 2010 . This is in recognition of the importance of the forest for global biodiversity conservation and sustainable development. The forest has the highest species diversity in the country with over 450 species of higher plants, 250 species of birds and several groups of organisms, most importantly the area is the largest forest block with unique wild populations of coffee. The wild populations of coffee are in the forest are the most genetically diverse , and unique, which don’t occur elsewhere in Ethiopia and the world” ካለ በሁዋላ አስተያየቱን ሲያሰፍር ደግሞ እንዲህ ብሎአል።
We are concerned of the impact on the site and biodiversity very strongly ( ተጽእኖው በጣም ያሳስበናል) ብሎአል።
የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ ታህሳስ 12 ቀን 2003 ዓም ለማእድን ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ደግሞ እንዲህ ብሎአል “ በቁትር መአ/220/20 ህዳር 08 ቀን 2003 ዓም በተጻፈ ደብዳቤ በኦሮምያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኢሉባቦር ዞን ያዩ ወረዳ ውስጥ ሊተገበር በታቀደው የኮል ፎስፌት ማዳበሪያ ኮምሌክስ ፕሮጀክት ላይ በአማካሪ ድርጅቱ የተሰጠ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽኖ ግምገማ ጥናት ሰነድ ላይ በተለይም ፕሮጀክቱ በያዩ ኮፊ ፎሬስት ባዮስፌር ሪዘርቭ ቦታ ላይ በተለየ ከማረፉ አንጻር ሙያዊ አስተያየት እንድንሰጥ በተጠየቅነው መሰረት ይህ ፕሮጀክት በያዩ ኮፊ ፎሬስት ባዮስቪር ዞን ውስጥ ማረፉ በብዝሃ ህይወት በተፈጥሮ ሃብቱ ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት በተጨማሪ በዩኒስኮ በተቀመጠው እና በሌሎችም አገራት ስምምነት በተደረሰበት መሰረት ይህ ይህ የባዮስቪር ዞን መዋል የሚገባው በአካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚደረግ ጥናትና ምርምር፣ ለመዝናኛና ለቱሪስት መስህብነት በመሆኑ ፕሮጀክቱ እዚያ ላይ ማረፉ ተቀባይነት የለውም ብሎአል።
ማእድን ሚኒስቴር ከኦሮምያ የደንንና አካባቢ ኢንተርፕራይዝ፣ ከአካባቢና የቡና ጫካ መድረክ እንዲሁም የአካባቢ መድረክ ከተባሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተሰጡትን አስተያየቶች ተንተርሶ ለፕሮጀክቱ መጀመር ፈቃዱን አልሰጠም።
የማእድን ሚኒስቴርና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ሃላፊነታቸውን በመወጣት ፕሮጀክቱ እንዳይጀመር ቢጠይቁም፣ ሜቴክ የሁለቱ ሃላፊ ሚኒስቴሮችን መመሪያ በመጣስ በህገወጥና በማን አለብኝነት ስራውን ጀምሯል። በህወሃቱ ጀኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ፣ የሲቪል የግንባታ ስራውን ለማሰራት ለህወሃት ደጋፊ ባለሃብትና በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢድናሞል የገበያ አዳራሽ ባለቤት ለሆኑት ለአቶ ተክለብርሃን አምባዬ የግንባታ ማህበር ከፊል ኮንትራት የሰጠ ሲሆን፣ ሁለቱ ድርጅቶች በገንዘብ የተነሳ ውዝግብ ውስጥ በመግባታቸው ስራው ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የደን ሽፋን በየጊዜው እየተመናመነ የመጣ ሲሆን፣ አገሪቱ ካሉዋት ጫካዎች ውስጥ የያዩ የደን ልማት አንዱና ዋነኛው ነው። በማእድን ሚኒስቴር የሚሰሩ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን፣ ኢሳት እና ሌሎችም የአገሪቱ ሚዲያዎች ደኑን ከውድመት ለመከላከል ድምጻቸውን ሊያሰሙ እንደሚገቡ አሳስበዋል።