ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-“በኢትዮጵያ ያሉ ሚንስትር ድኤታዎች ድምፅ አልባ እና ተሳትፎ የሌላቸው ደካማዎች ናቸው” ሲል የኢህአዴግ ጽ/ቤት የአመራር ግንባታ የመለስ ዜናዊ የአመራር ግንባታ ክፍል ያወጣው ደብዳቤ አመለከተ። ደብዳቤው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ያላቸውን ሚኒስትር ድኤታዎች ዘርዝሮ አስቀምጧል።
በአቶ አዲሱ ለገሰ የሚመራው እና ከፍተኛ የኢህአዴግ አባላትን ብቻ የሚያሰለጥነው የኢህአዴግ አመራር ማሰልጠኛ ክፍል የአመራሮችን አቅም በመገምገም በሚንስትር ድኤታ ደረጃ ያሉትን ብቻ ለይቶ በመጥራት ውይይት አካሂዷል፡፡ በዚህም በመሪነት ደረጃ ለኢህአዴግ አቅም መጎልበት አስተዋጽኦ ያላደረጉ እና ቀዳሚ መሆን ያልቻሉ ያላቸውን አካላትን ዘርዝሮ አስቀምጧል፡
በዝቅተኛ ደረጃ የተመደቡት የፊደራል ጉዳዩች ሚንስቴር ሚንስተር ድኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታ አቶ ወንዲራድ ማንደፍሮ፣ የኢፌድሪ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድኤታ አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ድኤታው አቶ ፉኢድ ኢብራሒም፣ የኢንዱስትሪ ሚንስትር ድኤታ ልዩ አማካሪ አህመድ ኑሩ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ድኤታ አቶ ሙልጌታ ሰኢድ ፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ድኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ የትምህርት ሚኒስትር ሚንስትር ድኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ፣ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ድኤታ አቶ ማህሙድ አህመድ ጋአስ ናቸው።
በመካከለኛ ደረጃ የተቀመጡት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ታደሰ ኃይሌ፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ድኤታ አቶ ጌታቸው ነጋሽ፣ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ድኤታ አቶ አህመድ ሽዴ እና የፍትህ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ናቸው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ባለባቸው የአቅም ውስንነት ምክንያት ወደ ሚንስትርነት ማእረግ ደረጃ ማደግ ስለማይችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠና በክረሙቱ ተከታታይ ወራት ያስፈልጋቸዋል ተብሎአል። ይህም ሁኖ መሻሻል ካላሳዩ ከስልጣናቸው ወርደው በምትካቸው በአዲሱ ሰው እንዲተኩ የኢህአዴግ አመራር ማሰልጠኛ ኢንስትትዩት በአሁኑ ስያሜው የመለስ አመራር ማሰልጠኛ አካዳሚ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ አስተያየታቻውን አስፍረዋል፡፡
የከፍተኛ አመራሩ ምደባ ግምገማ ኮሚቴ ተዋቅሮ በድክመት ፣ ጥንካሬ እና አማራጭ ተብሎ እየተለየ ሲሆን ፣ ከነድክመታቸው የሚያሰቀጥላቸውንና ወደ አመራር የሚያመጣቸውን አዳዲስ የፖለቲካ መሪዎች ስም ዝርዝር እና ግለ ታሪክ ተዘጋጅቶ እንዳለቀና እንደደረሰን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡