ሚኒስትሩ ፤ በቴሌ ሠራተኞች ጠንካራ ተቃውሞ ገጠማቸው

ሐምሌ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በአቶ  ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሰብሳቢነት የቴሌ ሠራተኞች በወቅቱ አገራዊ ጉዳይ ትናንት የጀመሩት ውይይት፤ በከፍተኛ ተቃውሞ እየቀጠለ እንደሚገኝ በስፍራው የሚገኘው የኢሳት ዘጋቢ አመለከተ።

እጅግ በርካታ የቴሌ ሠራተኞች በተገኙበት በዚህ ስብሰባ ላይ ተሳታፊዎቹ  ከሰነዘሯቸው ተቃውሞዎች አንዱ፤ “የኮንዶሚኒየም ቤት ለደሀው ህዝብ እንደሚሠራ ስትናገሩ ከቆያችሁ በሁዋላ አሁን ሲጠናቀቅ ለሀብታሞችና ለተወሰኑ ብሔር አባሎች እየመረጣችሁ መስጠታችሁን ደርሰንበታል” የሚል ይገኝበታል።

እንዲሁም፦”የትምህርት ፖሊሲውን ቀይራችሁ ጥራቱን በመግደል ትውልድ  ገደላችሁ፣ባለ ዲግሪ ድንጋይ ጠራቢ አፈራችሁ፣ እኛ ተርበን እናንተ ስለጠገባችሁ፤በምግብ ራሳችንን ችለናል ትላላችሁ! በሀገራችን ሁለተኛ ዜጋ ሆነናል። ሥራ ሆነ የሥራ ዕድገት ለማግኘት ግዴታ የ ኢህአዴግ አባል ሁኑ እየተባልን ነው”የሚሉ ተቃውሞዎችም ተሰንዝረዋል።

በስብሰባው ያልጠበቁት ተቃውሞ የገጠማቸው ሚኒስትሩ አቶ ደብረ-ጽዮን፤ የሚመልሱት ጠፍቷቸው በድንጋጤ ሲርበተበቱ መታየታቸው ታውቋል።

እንደ ኢሳት ወኪል ሚኒስትሩ  ችግሮች ለወደፊት ይሻሻሉ በማለት ከማድበስበስ በቀር ከተሰነዘሩት ጠንካራ ተቃውሞዎች  ለአንድኛቸው እንኳ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት አልቻሉም።

በድንጋጤ  የሚናገሩት የጠፋቸው ሚኒስትሩ፦ ሌላው ቀርቶ ፦ “ኢትዮጵያ ያለችበት አቋም አሁን ጥሩ  ነው” ማለት  ተስኗቸው ፦”ኢትዮጵያ ያላት ቁመና ጥሩ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ሚኒስትሩ ይህን ሲሉ ተሰብሳቢው ህዝብ እንደሳቀባቸውም ተመልክቷል።

በሌላ በኩል በዚሁ ስብሰባ ነፃ ግብዣ እንደነበረ የጠቀሰው የኢሳት ወኪል፤ ይሁንና ለአንድ ምሳ  በሰው 200 ብር ወጪ እንደተደረገ ሢታወቅ ተሰብሳቢው በሙሉ  በብስጭት፦” ይህ ብፌ 50 ብርም ይበዛበታል” በማለት ተቃውሞውን  ሲያሰማ እንደነበር ጠቁሟል።

“የህዝብ ገንዘብ ፤በኛ ምሳ ስም ወጪ  ተደርጎ መዘረፉ ያሳዝናል” ያሉት እነኚሁ  ተሰብሳቢዎች፤ ከአንድ ሰው ምሳ ላይ በትንሹ የ150 ብር ሙስና ተፈጽሟል የሚል ግምት እንዳላቸው ወኪላችን ያጠናቀረው ዘገባ ያመለክታል።   ስብሰባው አሁንም  እንደቀጠለ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide