ሙስና እና ፖለቲካ ብአዴንን እየፈተኑት ነው

መጋቢት ፳፯ (ሀያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-“ማንኛውም ሰው” ይላሉ አንድ የብአዴን ከፍተኛ አመራር ” ስለ እነ አቶ በረከት ክፉ ቢያወራ በደቂቃዎች ውስጥ ራሱን እስር ቤት ውስጥ ያገኘዋል፣ ባበህርዳር።”

በ9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ በተለመደው ቋንቋ ሙስና ወይም ጉቦኝነት የድርጅቱ ዋነኛው የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ነበር።

የብአዴን ነባር ታጋይ አቶ ህላዊ ዮሴፍ፣ እውን ከፍተኛውን አመራር የምንጠይቅበት ስርአት አለን?” ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ብዙዎች በዚያ መድረክ ይጠየቃል ብለው ያልጠበቁት ነበር።

አቶ ህላዊ ዮሴፍ፣  የአማራ ልማት ማህበር ሊ/መንበር በነበሩበት ጊዜ ፣ የድርጅቱን የሂሳብ ሰነዶች አቃጥለው ያለተጠያቂነት ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወሩ መደረጋቸው አንዳንድ የብአዴን አባላትን   ሲያብሰከስክ የቆየ ቢሆንም ፣ በኢህአዴግ 9ኛው ጉባኤ ላይ ባሳዩት ጠንካራ አቋምና ባቀረቡት ንግግር  ብዙዎቹ ተደስተዋል።  አስገራሚው ነገር ይላሉ የ ብአዴኑ ሰው ”  ከሽማግሌዎቹ የብአዴን  አመራሮች በስተቀር ሌሎች ወጣት አመራሮች ምንም ነገር ሳይናገሩ  ጉባኤው ተጠናቋል።  ወጣት አመራሮች እንደ ተራው አባል  ሁሉ “እናውቃለን፣ ብንናገር እናልቃለን ”  የሚሉ የመስለኛል ይላሉ አባሉ።

የባህርዳር ከተማ ህዝብ እና የብአዴን አባላት የሚያሰሙት የውስጥ ለውስጥ ተቃውሞ ማየል ያሰጋቸው  አቶ በረከት ስምኦንና አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ቁልፍ ሰዎች የሚሉዋቸውን፣ የክልሉን የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ የነበሩትን አቶ ከበደ ጫኔን እና የክልሉን የፍትህ ቢሮ ሀላፊ የነበሩትን አቶ ጌታቸው አምባየን ወደ ፌደራል መንግስቱ እንዲዛወሩ አደረጉ። አቶ ከበደ  ከጸጥታ ዘርፍ ሃላፊነት ወደ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒሰትርነት፣  አቶ ጌታቸው ደግሞ ከፍትህ ቢሮ ሀላፊነት በምክትል ከንቲባነት ማእረግ የመሬት ባንክ ሃለፊ ሆነው ተሾሙ።

ሁለቱ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ እንደተዛወሩ በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ታዋቂው ባለሀብት  ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት ገዝተው ቁልፉን አስረከቧቸው።

ባለሀብቱ በባህርዳር እምብርት ላይ የተገነባው የጋሳ ሆቴል ባለቤት ናቸው። አቶ በረከት በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት የዳሽን ቢራም ብቸኛ አከፋፋይ ናቸው። ደሻን ቢራንን ከ1995 ዓም ጀምሮ እንዲያከፋፍሉ ሲመረጡ ያለማንም ተቀናቃኝ ነው።  በተለምዶ አየር  ማረፊያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢም ፣ በተንጣለለ መሬት ላይ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል  እያስገነቡ ነው። በሁመራ ለሰሊጥ ምርት ፣  በቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ለተለያዩ የእርሻ ስራዎች የሚውሉ እጅግ ሰፊ መሬት አግኝተዋል። ከ5 በላይ ዩሮ ትራክተሮች፣ በርካታ ዶዘሮች፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሚኒባሶች እና ሌሎች በርካታ ድርጅቶች ያሉዋቸው ባለሀብት፣ ለርጅም ጊዜ በልብስ ሰፊነት ነበር የሚተዳደሩት።

ወጣት የብአዴን አመራሮችን ያሳሰበው ጉዳይ ግለሰቡ በአጭር ጊዜ ቱጃር መሆናቸው ሳይሆን፣ ሀብታቸውን ተከትሎ ያላቸው ፖለቲካዊ ጫና እየጎላ መምጣቱ ነው። በአቶ በረከት ፣ በአቶ አዲሱ እና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ትችት የሚያቀርቡ፣ እርሳቸውን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም የሚያነሱ የብአዴን አባላትም ሆኑ  የባህርዳር ነዋሪዎች፣ በምሽት ራሳቸውን ” የደህንነት ሹም በነበሩት አቶ ከበደ ጫኔ ቢሮ ውስጥ” ማግኘቱ የተለመደ ነው፣ እንደ ውስጥ አዋቂው የብአዴን ከፍተኛ አመራር። የክልሉን ፍትህ ቢሮ በበላይነት ሲዘውሩት የነበሩት አቶ ጌታቸው አምባየም የህግ ከለላ በመስጠት፣ ብቅ ብቅ የሚለውን የብአዴን ወጣት አመራር አንገቱን ያስደፉታል።

የክልሉ ምክር ቤት፣ የክልሉ ካቤኒ እና የክልሉ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ከህዝቡና ከብአዴን አባላት የሚደርሳቸው ጥቆማ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ፣ በጉዳዩ ዙሪያ መወያየት ጀመሩ። የክልሉ ገቢዎችም በባለሀብቱ በአቶ ሸጋው ላይ ክስ መሰረተ፤  ዳሸን ቢራን ሲያከፋፍሉ 15 ሚሊዮን ብር ቫት ለመንግስት መክፈል ሲገባቸው አልከፈሉም በማለት። አቶ ሸጋውም ተይዘው ታሰሩ። ወጣት የብአዴን አመራሮችም ግለሰቡ ከህግ በላይ አለመሆናቸውን በማሳየታቸው ተደሰቱ። ደስታቸው ግን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አልነበረም። በቫት የተከሰሰ ሰው ዋስትና እንደሌለው ቢታወቅም፣ አቶ ሸጋው ማታውን በ150 ሺ ብር ዋስ እንዲወጡ ተደረጉ፣ በሁለተኛውም ቀንም ክሱ መቋረጡ ተሰማ። ትእዛዙን የሰጠው ሰው ሳይታወቅ ቀረ፣ ወጣት የብአዴን አመራሮችም ሆድ ይፈጀው ብለው የውስጥ ትግላቸውን ቀጠሉ።

አቶ በረከት ዳሸን ቢራን በቦርድ ሰብሳቢነት ቢመሩትም፣ ለረጅም ጊዜ ስራ አስኪያጅ በመሆን  ያገለገሉት  አቶ ብርሀኑ አድማሱ ነበሩ። አቶ ብርሀኑ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በዳሸን ቢራ ላይ አሉታዊ ዘገባ አቅርቧል በማለት ፣ ዋና አዘጋጁ አቶ አማረ አረጋዊ ጎንደር ተወስዶ እንዲታሰር ያደረጉ ናቸው። ግለሰቡ በአቶ በረከት እና በአቶ አዲሱ  በእጅጉ ይመካሉ። ዊኪሊክስ ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ በአንድ የእራት ምሽት ላይ አንድ የአሜሪካ የፖለቲካ አታሼ ለአቶ ብርሀኑ እንዲህ ሲል ይጠይቃቸዋል” ለመሆኑ እርስዎ ተጠሪነትዎ ለማን ነው?” አቶ ብርሀኑም ” ለእግዚአብሄር” ብለው መለሱ። “ለአቶ በረከትና ለአቶ አዲሱ ሪፖርት አያደርጉም?” አሉዋቸው ደግመው፣ “በርግጥም ለሁለቱ ብቻ” ሪፖርት አደርጋለሁ።” አሉ። ዲፕሎማቱ ስለአቶ አማረ ሲያነሱባቸው ደግሞ ”  I can make or break anyone.  I have the right to kill” ( ማንንም እንደፈለኩ ማድረግ እችላለሁ፣ የመግደል መብት አለኝ።’ የአሜሪካው ዲፕሎማትም  አስተያየቱን በመጨረሻ ሲያሰፍር ” With this growth comes an increased sense of power and invincibility for the leadership of the brewery ” ፋብሪካው እያደገ ሲመጣ ስልጣንም፣ ማንም አይደፍረኝም ባይነትም ፣ በአመራሩ ዘንድ እያደገ መጣ”

ስራ አስኪያጁ አቶ ብርሀኑ በአቶ በረከት፣ በአቶ አዲሱ፣ በአቶ ከበደ፣ በአቶ ጌታቸው፣ በአቶ ታደሰ ካሳና በአቶ ሸጋው በተሰራው  ጎጆ ውስጥ አብረው የሚኖሩ ነበሩ። ግለሰቡ በርካታ ጠርሙስ ቢራዎች ያለአግባብ እንዲወጡ በማድረግ፣ የሙስናውን ጎጆ ሲያደራጁ ከቆዩ በሁዋላ፣ ለእርሳቸው የሚሰጠው ድርሻ እያነሰ መምጣቱን በመቃወም ከሌሎች አመራሮች ጋር መጨቃጨቅ ጀመሩ። አካሄዳቸው ያላማራቸው  እነ አቶ በረከት ” ማንም አይነካኝም፣ የመግደል መብት ተሰጥቶኛል” በማለት ሲፎክሩ የነበሩትን ግለሰብ በሙስና ከሰው እስር ቤት ወረወሩዋቸው። ለጊዜውም እፎይታ አገኙ።

በ9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የብአዴን ወጣት አመራሮች የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው፣ የነባር አመራሮችን ” ሙስናን እንዋጋለን” ዲስኩር ፈገግ እያሉ ይሰሙ ነበር። ህዝቡም አቤታቱን ማሰማቱን ቀጥሎአል፤ ወጣት አመራሮችም ታገሱ ይላሉ።

ባለሀብቱን አቶ ሸጋውን አፈላልገን በማግኘት ” ስለ እነ አቶ ጌታቸው አምባየ..”ልናነጋግሮት ነው ብንላቸው ” ንቀት በተሞላበት ሁኔታ ” ስልካቸውን ዘጉብን።

አቶ ሸጋውም ሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት ከዘገባው በሁዋላ ምላሻቸውን የሚሰጡ ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን ለመግለጽ እንወዳለን።