ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በአደባባይ ያጋለጡት ሚኒስትር ዴኤታ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተዘገበ

ታህሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሳምንታዊው ሰንደቅ እንደዘገበው ፤በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያለውን ብልሹ አሰራር እና ሙስና ከሳምንታት በፊት በይፋ ያጋለጡት  ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዳውድ መሐመድ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው  አቶ ዳውድ መሐመድ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በቅርብ የበላይ አለቃቸው ማለትም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ  በአቶ አሚን አብዱልቃድር እና በሌላዋ ሚኒስትር ዴኤታ በወ/ሮ ታደለች ዳለቾ መካከል  የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ   ለሰንደቅ ጋዜጣ በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ ከተገመገሙ በሁዋላ ነው።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምንጮች እንዳሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ሰሞኑን በተካሄደው በዚሁ  ግምገማ አቶ ዳውድ ከሚኒስትር ዴኤታ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ሆኗል።
አቶ ዳውድ መሐመድ  በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን የባህል ዘርፍን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲመሩ ቆይተዋል።
አቶ ዳውድ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በግልፅ የሚታየውን ሙስናና ብልሹ አሠራር በአደባባይ በመተቸታቸው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለሚታገሉ ኃይሎች ሁሉ አስደንጋጭ መልዕክት ያስተላለፈ ነው ሲሉ አንድ የመ/ቤቱ ባልደረባ አስተያየታቸውን ለጋዜጣው ገልጸዋል።

አስተያት ሰጪው አክለውም፦“ኪራይ ሰብሳቢዎች በክብር ተቀምጠው ሕገወጥ አሠራርን የሚታገሉትን  ባለሥልጣን ከኃላፊነት ማንሳት ምን ማለት ነው? ለሌሎችስ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው?” ሲሉም በአግራሞት  ጠይቀዋል።

አቶ ዳውድ ህዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም በወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ በመ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ስለተፈጠረው ችግር ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር እና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ግንባር በመፍጠር በመ/ቤቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን አድርገዋል በማለት ቅሬታቸውን ከመግለፃቸውም ባሻገር ይህንንም ቅሬታ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አሳውቀው መፍትሄ አለማግኘታቸውን በይፋ  ማሳወቃቸው ይታወሳል።