ሚያዚያ ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ ሙስናን እዋጋለሁ በሚል በጀመረው ዘመቻ፣በዝቅተኛ እርከን ላይ ያሉ አንዳንድ አመራሮችን ከስራቸው ላይ አንስቶ ወደ ሌሎች ቦታዎች በመመደብ፣ በተወሰኑት ላይ ደግሞ ክስ በመመስረት ከህዝብ የሚደርስበትን ነቀፋ ለማብረድ እየሞከረ ቢሆንም፣ በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ የወሰደው እርምጃ ባለመኖሩ ፣ በህዝቡ ዘንድ ያለው ቅሬታ አሁንም ከፍተኛ ነው።
በመጀመሪያዎቹ የስልጣናት ወራት፣ ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆናቸውን ሲናገሩ የነበሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የሁዋላ ሁዋላ ለእረፍት እና ውበትን ለመጠበቅ በሚል የግል አውሮፕላን ተከራይተው ጀርመን መሄዳቸው; ከፍተኛ አመራሩን የያዙት የኢህአዴግ ሹሞች አንዳቸውም ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ አለመሆናቸውን ወይም ከመካከላቸው ሙስናን ለመዋጋት ፍላጎት ያለው ሰው አለመኖሩን እንደሚያሳይ ታዛቢዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ኢሳት ከዚህ ቀደም የአቶ መለስ ዜናዊ እህት ያስገነቡትን ዘመናዊ ሆቴልና መኖሪያ ቤት እንዲሁም አባዱላ ገመዳ የሚያስገነቡትን ሆቴል በቪዲዮ ማቅረቡ ይታወቃል። የኢሳት ወኪል ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ሰዎች ጋር በመመካከርና በእነሱ ድጋፍ አሁንም የተለያዩ ባለስልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች የሚያስገነቡዋቸውን ቤቶች በቪዲዮ በመቅረጽ ልኳል። ካለው የደህንነት ጥበቃ አንጻር በዘመናዊ ካሜራ ቤቶችን ቪዲዮ አንስቶ ለመላክ ባይቻልም፣ ተመልካቾቻችን ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ በዛሬው የዜና እወጃችን የጄ/ል ፍሰሃ ኪዳነማርያም መስፍንን፣ የጄ/ል ዮሃንስ ገብረመስቀልን፣ የጄ/ል ሳሞራን፣ የገዛኤ ረዲን፣ የባጫ ደበሌን ፣ የጄ/ል ገብረመድህንን ፣ የመቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን፣ የአምባሳደር ሙሃመድ ድሪርን፣ የአባ ዱላ ገመዳን እና የሌሎችንም መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች አቅርበናል።
“በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝብ በርሃብ በመጠቃቱ አለማቀፍ እርዳታ እየተለመነ ነው። ነጋዴዎች ግብር ጨመረብን በሚል ተቃውሞ እያሰሙ ነው። የመንግስት ሰራተኞች የሚከፈለን ገንዘብ ህይወታችንን በአግባቡ መምራት አላስቻለንም እያሉ ነው። ፖሊሶችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ቤተሰቦቻችን ለመርዳት የሚያስችል ክፍያ አናገኝም በማለት የቻሉት ስራቸውን ለቀው እየጠፉ ሲሆን፣ በከተሞች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ፖሊሶች፣ ከዘራፊዎች ጋር በመመሳጠር፣ በከተሞች እየተስፋፋ ከመጣው ወንጀል ጀርባ እጃቸው እንዳለበት የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአገሪቱ ያለው የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እየናረ ሲሆን፣ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉት ደግሞ በበቂ ሁኔታ አልተገኙም። ህዝቡ በኑሮው ውድነት እየተሰቃየ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አሁንም ጥቂት የመንግስት ባለስልጣናትና ከእነሱ ጋር የተሻረኩት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየዘረፉ እንዲሁም በዙሪያው ያሉትን አርሶአደሮች እያፈናቀሉ ህንጻዎችን እየገነቡ ነው “ በማለት አስተያየቱን የገለጸው ወኪላችን፣ አሁን ባለው የቤቶች ግምት፣ የባለስልጣናቱ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ ዝቅተኛው ግምት 50 ሚሊዮን ሲሆን፣ ብዙዎቹ በመቶ ሚሊዮኖች ዋጋ እንደ ሚጠራባቸው ከባለሙያዎች መረዳቱን ገልጿል ።
በኢትዮጵያ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ደሞዝ ከ6 ሺ ብር እንደማይበልጥ ይታወቃል።