ታህሳስ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ላለፈው አንድ አመት የጁመዓን ጸሎት ተከትሎ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል።
ኢትዮጵያውያኑ መንግስት ድምጻችን ይስማን፣ የታሰሩ መሪዎች ይለቀቁ፣ መንግስት የለም ወይ በማለት ድምጻቸውን አስምተዋል።
ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ በተካሄደበት በዚህ ተቃውሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በአንዋር መስጊድና በውጭ በመሆን ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በሴቶች መስገጂያ በኩል የጸጥታ ሀይሎች 11 የሚሆኑ ሴቶችን ይዘው ማሰራቸው ታውቋል። ታስረዋል ስለተባሉት ሴቶች በመንግስት በኩል ለማረጋገጥ ብንሞክርም አልተሳካልንም። የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በእስር ላይ የሚገኙትን የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን የፍርድ ቤት ጉዳይ ለመከታተል በልደታ ፍርድ ቤት የተገኙ ሙስሊም ሴቶች ተመርጠው መታሰራቸው ይታወሳል።
የዛሬው ተቃውሞው አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን የሙስሊሙን ጥያቄ በተመለከተ የሰጡትን ቃለምልልስ ለመቃወም ያለመ ነው። አቶ ሐይለማርያም በሙስሊሞች ጥያቄ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የሙስሊሙ ጥያቄ የጥቂቶች መሆኑንና አብዛኛው ሙስሊም መብቱ ተከብሮለት እየኖረ መሆኑን ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት የሙስሊሙን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ ሆኖ አለመገኘቱ የአሜሪካን መንግስት ሳይቀር እያሳሰበ መምጣቱ ታውቋል።
የአሜሪካ ልኡካን ቡድን በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመመላለስ የመንግስት ባለስልጣናት የሙስሊሙን ድምጽ እንዲሰሙ እየወተወቱ ነው።
በተመሳሳይ ዜና እሁድ በቃሊቲ የሚደረገውን የእስረኞች ጉብኝት የጸጥታ ሀይሎች ለማወክ ቢሞክሩ ህብረተሰቡ በትእግስት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲያሳልፈው አዘጋጆች ጥሪ አቅርበዋል። በስፍራው የሚገኙ የአዲስ አበባና የአካባቢው ነዋሪዎች በሚይዙዋቸው ሞባይሎች፣ ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ ፖሊሶችን በቪዲዮ ቀርጸው እንዲያስቀሩ ጠጥቀዋል።