ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ አካሄዱ

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው በተለምዶ ጀርመን መስጅድ ውስጥ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። “የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ!” በሚል ምእመናኑ መፈክሮችን በማንገብ በግቢው ውስጥ ሰላማዊ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። ምእመናኑ ” የነቃ ህዝብን ያሸነፈ አፈና የለም! ሰላማዊ ያደረገን የአሚሮቻችን ቃል እንጂ የአምባገነን ጡጫ አይደለም! ሰላም ከነሳችሁን ተመሳሳይ ኑሮ እንድንኖር ታስገድዱናላችሁ! ትግላችን ይቀጥላል! ፍትሕን ቀበሯት! ድምጻችን ይሰማ!” የሚሉ መፈክሮችን በጨርቅ እና በወረቀት ጭምር ይዘው ወጥተዋል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚሰግዱባቸውን መስኪዶች በመቀያየር ገዢው ፓርቲ አስቀድሞ እርምጃ እንዳይወስድ ለማድግ መቻላቸው፣ የመንግስትን የስለላ አቅም ድክመት ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን የድምጻችን ይሰማን ሚስጢር የመጠበቅ ችሎታም የሚያሳይ ነው ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።