መጋቢት ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጋምቤላ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ታሪካዊውየሐመረ ኖኅ ኪዳነምህረት ጽላት ማነታቸው በማይታወቁ ግለሰቦች መዘረፉን የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ምእመናን ገልጸዋል።
የደብሩ ካህናት በበኩላቸው ከየካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ቀን ጀምሮ ታቦቱ ከመንበሩ አለመኖሩን አሳውቀዋል፡፡
በ1941 ዓ.ም. በቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ሀይለስላሴ እንደተሰራ የሚነገርለት ይህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ታቦቱ በቅርስነት ተይዞ ጥበቃ ሊደረግለት ሲገባ ያለበት አድራሻ አለመታወቁ እንዳሳዘናቸው ምእመናኑ ይናገራሉ፡፡
ጽላቱ በመንበሩ አለመኖሩን አስቀድመው ያወቁት የሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል አተዳዳሪ በበኩላቸው ”ታቦቱ የት ገባ?” ብለው ቄስ ገበዙን ሲጠይቋቸው ቄሰ ገበዙ “እኔን ለምን ትጠይቁኛላችሁ?ሥራ አስኪያጁን ጠይቁ” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎብናል ሲሉ ምእመናኑ ተናግረዋል፡፡
እነኚሁ የጽላቱ መጥፋት ያሣሰባቸው ምእመናን መጋቢት 13 እና 14 ቀን 2009 ዓ.ም ጉዳዩን አስመልክቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤትቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
ጽላቱ የሚቀመጥበት መንበር ባዶ መሆኑን የሚያሳይ በወቅቱ የተቀረፀ የቪዲዮ ምስል በአባሪነት ማቅረባቸውን የገለጹት ምእመናኑ ፣ ጽላቱ በመንበሩ ላይ ተገኘ ቢባል እንኳ ዕድሜ ጠገብ ጽላት መሆኑን ለይተውበሚያውቁ ካህናት ታይቶ መረጋገጥ እንደሚኖርበት አሣስበዋል።
ስለጉዳዩ የሚያውቁት መረጃ እንዳለ የተጠየቁት የማህበረ ቅዱሳን አመራር ዲያቆን አብይ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላለቸው በመጥቀስ፤ ሆኖም ይህ ጉዳይ በዋናነት የሚመለከተው የአጥቢያውን ደብር እንጂ ማህበረ ቅዱሳንን እንዳልሆነ አስረድተዋል።