መጋቢት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተለያዩ ክልሎችን የሚሸፍነው ሪፖርት፣ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ዝርዝር ጥቃቶችን አቅርቧል። በትግራይ ክልል በአጽቢወንበርታ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመድረክ ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ወ/ገብርኤል ኃይሉ የዕጩነት መታወቂያ እንደያዙ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ የአስር ወራት የእስራት ቅጣት ተፈርዶባቸዋል፡፡
“በቆላ ተንቤን ወረዳ በወርቅ አምባ ምርጫ ክልል የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ብርሃን ንጉስ ተክለእግዚም በተመሳሳይ ሁኔታ የዕጩነት መታወቂያቸውን እንደያዙ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ የሶስት ዓመት የእስራት ቅጣት ተፈርዶባቸዋል፡፡”
” ወ/ሮ ቤራይ ገብሩ የሚባሉ በሁመራ ምርጫ ክልል የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ደግሞ ከታሰሩ በኋላ ተፈትተዋል፡፡ የአቶ ወ/ገብርኤል ኃይሉ የእርሻ መሬትም ተነጥቆ የሕወሐት አባላት ለሆኑ ወጣቶች ተሰጥቷል፡፡ “
በሁመራ ምርጫ ክልል የአረና/መድረክ አባል የሆኑት ቄስ ህሉፍ ካህሳይና በቆላ ተንቤን የአረና/መድረክ አባል የሆኑት አቶ ዜናዊ አስመላሽም በፖሊስ፣ በኢህአዴግ ካድሬዎችና በአከባቢ ሚሊሺያዎች ተደብድበው ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡
በደቡብ ክልል ደግሞ፣ በወላይታ ዞን በዳሞት ጋሌ ቁጥር 2 ምርጫ ክልል የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ታዲዮስ ባዴቦ የኢህአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች የመድረክን የምርጫ ምልክትና ፖስተሮች ከተለጠፈበት እያወረዱ መቅደዳቸውን አስመልክቶ ለምርጫ ክልሉ ጽ/ቤት አቤቱታ በማቅረባቸው የቀበሌው አመራሮችና ታጣቂዎች ወደ ቀበሌ ጽ/ቤት ከወሰዱዋቸው በኋላ እዚያው አስመሽተው ልብሳቸውን አስወልቀው ሲደበድቧቸው ከቆዩ በኋላ ከምርጫ ውድድሩ እንዲወጡና የመድረክ ፖስተሮችንም እንዳይለጥፉ በማስጠንቀቅ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ላይ ከቀበሌው አውጥተው ለቋቸዋል፡፡
‘በሲዳማ ዞን በባንሳ ምርጫ ክልል የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ታሪኩ ሪባቶም የዕጩነት መታወቂያቸውን እያሳዩ በፈጠራ ክስ ተይዘው እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡ በዚሁ ዞን በዱባ ምርጫ ክልል የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ በሾላ ገቢሶ ዕጩነታቸው ይፋ እንደሆነ ለብዙ አመታት ሲያርሱ የኖሩትና የቡናና የእንሰት ተክል ያለበት የእርሻ መሬታቸው ለደን እንፈልገዋለን ተብሎ ተከልሏል፡፡’
በካፋ ዞን በፈለገ ሰላም ምርጫ ክልል የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ አትሽ ወ/ኢየሱስ የ16 ዓመት ልጅ ገበያ ሲሄድ በፖሊስ ተይዞ አድራሻው እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡
በዚሁ የምርጫ ክልል ደበለ በሚበል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑና ሌላ የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት የአቶ አለማየሁ አደሬን ባለቤት ፖሊሶችና የቀበሌ አመራሮች በቤታቸው ውስጥ አስረው ፣ ሶስት ሳጥን ሙሉ ልብሶችና በውስጡ የነበረ ገንዘብ፣ አልጋ፣ ወንበሮችና የጣውላ እንጨቶችን ወስደውባቸዋል፡፡
በጨታ ወረዳ የገሚቻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን ኃይሌ፣አቶ ወንድሙ ወዳጆ፣አቶ አዲሱ ጫረቶ፣ አቶ ሚጣቶ የርጋዮና አቶ በቀለ ወዳጆን የወረደው አስተዳደር የሚሊሺያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሳሁን መንገሻ የፓርቲ አባልነት መታወቂያቸውን ተነጥቀው ከታሰሩ በሁዋላ ተለቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወራ ጃርሦ ምርጫ ክልል በምርጫ ክልሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት መምህር በላይ ዘለቀ በጎሃፅዮን ከተማ በ28/06/2007 ዓም ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ላይ በፖሊሶች ክፉኛ ተደብድቧል፡፡
በዚሁ ምርጫ ክልል የኦሮሚያ ክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ጌቱ ዳዲ በወራ ጃርሶ ወረዳ ቱሉ ሚልክ ከተማ በ20/10/2007 የምርጫ ቅስቀሳ በራሪ ወረቀት በማሰራጨት ላይ እያለ በፖሊሶችና በወረዳው ካብኔ አባላት ክፉኛ ተደብድቧል፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን በግንደበረት ወረዳ ምርጫ ክልል በምርጫ ቅስቀሳ የተሳተፉና የኦፌኮ/መድረክ አባላት የሆኑትን ተማሪ ደጀኔ ዳባ፣ ተማሪ ደሞዛ፣ ተማሪ ጉታ ሀጫሉ፣ ተማሪ ግርማ እና ሌሎችም በርካታ ተማሪዎችና ሌሎች ደጋፊዎቻችን በወረዳው ፖሊሶችና ታጣቂዎች ተደብድበዋል፡፡
በምሥራቅ ሀረርጌ ጋራሙለታ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በዕጩነት የቀረቡት አቶ ጃፋር መሀዲ ተደብድበው የመመዘገቢያ ወረቀትና ገንዘባቸውን ተቀምተዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም በተመሳሳይ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ሳይመዘገቡ ቀርተዋል፡፡
በኢሉባቦር ዞን በመኮ ምርጫ ክልል የኦፌኮ/መድረክ ቢሮ ተሰብሮ በውስጡ የነበሩ ንብረቶች ተዘርፈዋል፡፡
መድረክ በርካታ ችግሮችን ዘርዝሮ በማቅረብ ምርጫ ቦርድ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል። እንግሊዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንደሌሉ በመግለጽ፣ በዚህ አመት ለመንግስት ልትሰጠው የነበረውን ቋሚ እርዳታ አቋርጣለች። የአውሮፓ ህብረትም በኢትዮጵያ ምርጫ ተስፋ በመቁረጥ የዘንድሮውን ምርጫ አይሳተፍም። ገዢው ፓርቲ በምርጫው ይፎካከሩኛል ብሎ የሰጋውን አንድነት ፓርቲን ማፍረሱ ይታወቃል። በሰማያዊ እና በመድረክ ላይ የሚደርሰው ጫናም በተመሳሳይ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሎአል።