ኢሳት ( ነሃሴ 25 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ(መድረክ) የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ የ15 ዓመት ግምገማ በማለት ያወጡትን መግለጫ “ህዝቡ ለሚያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቂዎች ምላሽ የማይሰጡ” በማለት መግለጫ አወጣ። በአገሪቱ ለተከሰተው ችግር ኢህአዴግ ሃላፊነቱን እንዲወስድም ጠይቋል።
መድረክ ነሃሴ 23 ቀን 2008 ዓም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ ወደጎን የተወ፣ ህዝቡ አምግባገነናዊ ስርዓቱን ለመቃወም እያደረገ ያለውን ጥረት ያልተገነዘበ በማለት ያጣጣለው ሲሆን፣ ከካድሬ ሹመኞች ግምገማና ለማስመሰል የሚካሄድ ብወዛ ውጭ የተለየ ለውጥ እንደማይመጣ አስታውቋል።
ኢህአዲግ ለችግሮቹ ብቻዬን መፍትሄ አገኛለሁ ማለቱ ለሌላ ጥፋት መዘጋጀት እንደሆነ የገለጸው የመድረክ መግለጫ የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች የችግሩ ፈጣሪ በሆነው ኢህአዴግ መፍትሄ ያገኛሉ ብሎ እንደማያምን አስታውቋል።
መድረክ ወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ባወጣው በዚህ መግለጫ በህዝብ የተነሱ የሰብዓዊና ዴሞክራዊሲያዊ መብቶች መከበር፣ የነጻነትና ፍትህ ጥያቄ፣ ባልመረጥናቸው ሰዎች አንተዳደርም የሚሉ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን እንደሚያምን አስታውቆ፣ ኢህአዴግ ምላሽ ብሎ ያስቀመጠው መፍትሄ ከጥያቄዎች ክብደት አንጻር ምንም የማይመጥንና ከኢህአዴግ ልምድ እንደታየው ወደፊትም ተስፋ እንደማይኖረው አስታውቋል።
በተለይም የህዝቡን የተቃውሞ እንስቃሴ ኢህአዴግ “ልማቱ ያስከተለው ነው” በሚል ምላሽ መስጠቱ እጅግ እንዳስገረመው ገልጿል።
እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች ህዝባዊ መሰረት እንዳላቸው እየታወቀ ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ ሻዕቢያዎች፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በማለት መግለጽ ህዝብን መናቅ እንደሆነ የገለጸው መድረክ ከዚህ ይልቅ ወደ ትክክለኛው መፍትሄ እንደሚያዋጣ አሳውቋል። መድረክ መፍትሄ በማለት ያስቀመጣቸው የህዝቡ ህገ-መንግስታዊ መብት ማክበር፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የታሰሩ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ ህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ማቆም፣ ለተፈጠረው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂው መንግስት በመሆኑ ካሳ እንዲከፈል፣ የጉዳት መጠኑ በገለልተኛ አለም አቀፋዊ አካል ተቋቁሞ እንዲጣራ ማድረግና ገዢው ፓርቲ ከሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ ድርድር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ይገኙበታል።
የኢህአዲግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተ ምንም አይነት የጥሪም ሆነ ድርድር ጥያቄዎች አለማቅረቡ የሚታወስ ነው።