መከላከያ ኦዲት እንዳይደረግ የሚያስችል አዋጅ ተረቀቀ

ጥቅምት ፳፯(ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ሰንደቅ እንደዘገበው በ2004 በጀት ዓመት ባልተሟላ ሰነድ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ባላይ ወጪ በማድረጉ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጠንካራ ትችት የቀረበበት የመከላከያ ሚኒስቴር የሒሳብ መዛግብቱን ዋናው ኦዲተርን ጨምሮ ለማንኛውም አካል ሚስጢር ማድረግ የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።

አዲሱ የመከላከያ ሠራዊት ረቂቅ አዋጅ ሰነድ በአንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት አገራዊ ጥቅምንና ደህንነትን ለመከላከል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጢር ብሎ የሰየማቸውን የሰው ኃይል ፕሮፋይል፣ የሒሳብ መዝገቦችና ሰነዶች እና የክፍያ ማስረጃዎች ለማንም አካል እንዳይገለጹ የማድረግ ስልጣን ተሰጥቶታል።

በአንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ሚኒስቴሩ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸው ለአገር መከላከል ዓላማ የሚውሉ ዕቃዎችና መሳሪያዎች ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ በነጻ እንደሚያስገባ ተፈቅዶለታል። ዕቃዎቹን እንዲያስፈትሽ ወይም ሰነዶቹን እንዲያስመረምር እንደማይገደድም ተደንግጓል።

የመከላከያ ተቋማት በሠላም ጊዜ የሚኖራቸውን የማምረትና አገልግሎት የመስጠት አቅም ለገቢ ማስገኛ ተግባር እንዲውል በማድረግ የሚገኘውን ገቢ፣ ለመከላከያ ጠቀሜታ የማያስፈልጉ ንብረቶችን በማስወገድ የሚገኘው ገቢ፣ በተቆጣጣሪ ባለስልጣንነት ከሚመራቸው ድርጅቶች የሚገኘውን የትርፍ ድርሻ እና ከሠላም ማስከበር ስምሪቶች የሚገኘው ገቢ በዋናው ኦዲተር ወይም እርሱ በሚሰይማቸው ኦዲተሮች በየዓመቱ እንዲመረመር እንደሚያደርግ በረቂቅ አዋጁ መደንገጉን ጋዜጣው ዘግቧል።

የፌዴራል ዋናው ኦዲተር ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ማጠናቀቂያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2004 ዓ.ም የኦዲት ሪፖርት መሰረት የመከላከያ ሚኒስቴር ባልተሟላ ሰነድ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ካደረጉ ዘጠኝ ያህል የመንግስት ተቋማት መካከል 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በማስመዝገብ የላቀ ድርሻ መያዙ ይፋ ከተደረገ በኋላ የመከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ሹማምንት ሪፖርቱን ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ጋዜጣው አስታውሷል።

በህወሀት ታጋዮች ቁጥጥር ስር የሚገኘው መከላከያ ሚኒስቴር ወጪውን በጄኔራል ኦዲተር እንዳይመረመር ለማስደረግ መቻሉ፣ በሚኒስቴሩ ውስጥ የሚታየውን ገደብ የለሽ የገንዘብ ዘረፋ እንደሚያባብሰው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ደፍሮ መከላከያን እስካሁን ለመመርመር አልቻለም። አብዛኛዎቹ የህወሀት ጄኔራሎች በመከላከያ ስም ከቀረጽ ነጻ በሚያስገቡዋቸው እቃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀብት ጣራ ላይ እንዲቀመጡ እንዳደረጋቸው ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል።