መከላከያ ሰራዊት በቦረና ሚኦ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ተኩስ ከፍቶ አንድ ሰው ሲገድል ሶስት አቆሰለ

ኢሳት (ሃምሌ 20 ፥ 2008)

በቦረና ዞን ሚዖ ወረዳ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በህዝብ ላይ በከፈቱት ተኩስ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የአይን ምስክሮች ለኢሳት ገለጹ። ማክሰኞ ዕለት በአካባቢው የመብት ጥያቄ በአደባባይ መነሳቱን ተከትሎ ረቡዕ ከተማዋን የተቆጣጠሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በእርቀት ተኩስ አንዲት የመንገድ ላይ ቸርቻሪም ሰለባ መሆኑ ታውቋል።

ማክሰኞ ዕለት በሚዖ ወረዳ ኩሉቡማ ከተማ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ገልጿል ፥ ጥያቄም አቅርቧል።

“በወያኔ አንተዳደርም፣ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ የታሰሩ ታሳሪዎች ይለቀቁ፣ ለሶማሊያ ክልል ተላልፎ እንዲሰጥ የተወሰነው ጉፋላይ የተባለው ቦታ አይሰጥብን” የሚሉ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ቀርበዋል።

ይህ ተቃውሞና ጥያቄ በማግስቱም ሊቀጥል ይችላል በሚል በአካባቢው ከሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ረቡዕ ዕለት ወደ ከተማዋ ገብተዋል። ምንም እንቅስቃሴ ባልነበረበት ሁኔታ የተወሰኑ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው በመታየታቸው ብቻ ተኩስ መከፈቱም ተመልክቷል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች በተለቀቀ ቪዲዮ ጭምር ማየት እንደተቻለው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በኩሉብማ ከተማ ህዝብ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ተኩስ ከፍተዋል። በዚህ ተኩስ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከቆሰሉት ውስጥ አንዱ የከተማዋ ነዋሪ ያልሆነ ለስራ ጉዳይ የመጣ እንደሆነም ታውቋል።

ሌላኛዋ የቆሰለችው በጎዳና ላይ ንግድ የምታካሄድ እንደሆነች የተገለፀ ሲሆን፣ ሶስቱም ሰለባዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

በህዳር ወር የኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለ6 ወራት ያህል ከቀጠለ በኋላ መቀዝቀዙ ሲታወስ፣ አሁን እንደገና እያገረሸ ይገኛል። በተለይ በአርሲ ሁኔታው እየተባባሰ ሲቀጥል ቦረና ላይም እንቅስቃሴው መታየት ጀምሯል።