ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 1/1997 ዓ.ም. ‹‹ድምፃችን ይከበር›› ብለው አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ የተጨፈጨፉበትን ዕለት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሰኔ 3/2004 ዓ.ም. በጽ/ቤቱ ሻማ በማብራትና የተፈፀሙትን ዘግናኝ ድርጊቶች የሚያስታውሱና የሚያወግዙ ጽሁፎችን በማቅረብ አስቦ ውሏል፡፡
አቶ ተስፋዬ ታሪኩ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ተቃውሞቸውን ለማሰማት ወደ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አስቃቂ የግድያ እርምጃ በማስታወስ ፕሮግራሙን በህሊና ጸሎት አስጀምረዋል፡፡ አያይዘውም ከሰባት ዓመት በፊት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ውድ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ሰማእታትን መዘከር የትግሉ አንድ አካል እንደሆም ተናግረዋል፡፡ በመቀጠል ገጣሚ ስለሺ ገዛህኝ ‹‹ደርሳለች ጊዜዋ›› የሚል ቀስቃሽ ግጥም ለታዳሚዎች አስደምጠዋል፡፡ወጣት የእዮብዘር ዘውዴ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል ‹‹ሰኔ 1/1997 ዓ.ም በታሪክ ምእራፍ ላይ›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርቧል፡፡ በጥናታዊ ጽሁፉ 1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለየ ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ዓበይት ክንዋኔዎች የተካሄዱበት ዘመን መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በተለይም በኢህአዴግ እና በቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲዎች ስለተጠሩት የሚያዝያ 29 እና 30 ቀን 1997 ዓ.ም. ህዝባዊ ሰልፎች፣ ሃገር አቀፍ ምርጫው ስለ ተካሄደበት ግንቦት 7/1997 ዓ.ም. እና ንጹሃን ዜጎች በአደባባይ በግፍ ስለተጨፈጨፉበት ስለ ሰኔ 1/1997 ዓ.ም. አትቷል፡፡ የምርጫ ውጤት ገና ሳይጠናቀቅ ገዥው ፓርቲ ‹‹መንግስት ለመመስረት የሚያስችለኝን ድምፅ አግኝቻለሁ›› ብሎ ማወጁን፣ ተከትሎ የህዝብ ቁጣ መነሳቱ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መግለጫዎች በሬድዮና በቴሌቪዥን እንዳይተላለፉ መከልከላቸው በራሱ ውጥረቱን አባብሶት እንደነበረ አቶ የእዮብ ዘር ዘውዴ በጽሁፉ አሳይቷል፡፡ የምርጫ ማጣራቱ ሂደት ፍታዊ አለመሆንም ሌላው አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ አብራርቷል፡፡
ሰማእታቱን ለማስታወስ የተዘጋጀውን የ7 ቁጥር ቅርጽ ያለውን ሻማ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ረጅም ዘመን የታገሉት አንጋፋው አባል አቶ ከበደ ጣሰው መለኮሳቸውን ዘጋቢአችን ገልጧል። በዚህ ዝግጅት ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጂነር ሐይሉ ሻውል አልተገኙም። ኢንጂነር ሀይሉ በህመም ምክንያት በፕ/ር አስራት የሙት አመት ዝግጅት ላይም አልተገኙም።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide