መንግስት የአገሪቱን ችግር በሃይል ለመፍታት በመሞከሩ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው ሲል ኦፌኮ ገለጸ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ/ም) የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ባወጣው መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያገራችንን ችግር እያባበሰ ስለሆነ መንግስት አዋጁን አንስቶ ከሃቀኛ ተቃዋሚዎች ጋር ድርድር እንዲያካሂድና ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር አሳስቧል።
ከዚህ በፊት በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ዓይነት ከ700 ሺ በላይ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ተዘዋውሮ ሰርቶ የመኖር መብቱ ተጥሶ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል እና አካባቢው እንዲፈናቀሉ መደረጉን፣ በቅርብ ጊዜ በምስራቅና ምዕራብ ሃሀርጌ በጨለንቆ፣ በአወዳይና በሃመሬሳ ወዘተ በርካታ ዜጎች መገደላቸውንና እንዲሁም በሞያሌ ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በአሳዛኝ ሁኔታ የዜጎች ህይወት መጥፋቱን ኦፌኮ ጠቅሷል።
መንግስት ግድያና እስራት፣ ህዝብን ከህዝብ ጋር ማጋጨት በአስቸኳይ እንደቂኦም እንዲያደርግ፣ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፣ አሳተፊ የሆነ የድርድር መድረክ ተከፍቶ ለአገሪቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቋል።