ጥር ፱ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ ብድር የሚሰጡ 2 ባንኮችን ጨምሮ 17 የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት ስራዎችን ለተወሰኑ የቻይና ኩባንያዎች ብቻ እየሰጡ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተከትሎ ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር መልስ መስጠቱን ሪፖርተር ዘግቧል።
ጋዜጣው እንዳለው መንግስት ቅሬታዎችን ለማስተካከል ቃል ገብቷል። መንግስት የግዢ ስርአት እንደሚዘረጋና የመሰረተ ልማት ተቋማት ኮንትራት እንደ አዲስ እንደሚያዋቅር ገልጿል።
ሚኒስቴሩ አንዳንድ የመንግስት የልማት ድርጅቶችንም መውቀሱን ጋዜጣው ዘግቧል። ከእነዚህም መካከል መብራት ሃይል አንዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሥራ አፈጻጸማቸው ደካማ ለሆኑ ኩባንያዎች ሥራ በመስጠቱ ምክንያት፣ ተስፋ የተጣለባቸው ፕሮጀክቶች ደካማ አፈጻጸም ባላቸው ኩባንያዎች እጅ እንዲወድቁ በመደረጉ ፕሮጀክቶቹ በታለመላቸው ጊዜ ውስጥ አለመጠናቀቃቸውን ገልጿል።
“ግልጽ ባልሆነ መንገድ ለተመሳሳይ ኩባንያዎች ሥራ እየተሰጠ ከመሆኑም በላይ፣ ሥራ ያገኙት ኩባንያዎች ሌሎች ኩባንያዎችን እየገፉ በብቸኝነት የኮርፖሬሽኑን ሥራ እየተቆጣጠሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡” ብሎአል ጋዜጣው።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኮንትራት አስተዳደር ጥንካሬው ባይታማም፣ በአማካሪ ድርጅት መረጣ ላይ ወቀሳ እንደቀረረበት ዘገባው ያመለክታል።
በተመሳሳይ ዜናም የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከስምንት ዓመት በፊት ለቻይናው ኩባንያ ሲኖ ኃይድሮ ሰጥቶት የነበረውን የጨሞጋ ያዳ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክትን መቀማቱን ጋዜጣው ዘግቧል።
ሲኖ ኃይድሮ ከ7 አመታት በፊት የጨሞጋ ያዳ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በራሱ ወጪ ገንብቶ ለማስረከብ ውል ቢዋዋልም፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሳይችል ቀርቷል። የቻይናው አግዚም ባንክ 278 ሜጋ ዋት ሃይል ለሚያመነጨው ፕሮጀክት 555 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ተስማምቶ ነበር።
የጨሞጋ ያዳ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በ ደብረ ማርቆስ ከተማ መውጫ ላይ ይገኛል፡፡