መንግስት የባንዲራ ቀንን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ጀምሯል።

መስከረም ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከሚፈስባቸው የመንግስት ክብረ በአላት መካከል አንዱ የሆነው የባንዲራ ቀን ዘንድሮም ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓም በአዲስአበባ ስታዲየም በድምቀት እንደሚከበር መንግስት አስታውቋል።

“በሕዝቦች ተሳትፎና ትጋት ድህነትን ድል በመንሳት ብሔራዊ ክብሯን እና ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ ከፍ በማድረግ ላይ ያለች ሀገር!” በሚል መሪ ቃል  ለ7ኛ ጊዜ በሚከበረው በዚህ በዓል ላይ ከአዲስአበባ ከተማ ከየወረዳው ሕዝቡ በተዘጋጀለት አውቶቡሶች ወደስታዲየም በማቅናት

በደመቀ ሁኔታ በልማት የተገኙ ድሎችን በመዘከር ይከበራል ተብሏል።

አቶ አባዱላ ገመዳ በቅርቡ በዓሉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የያዝነው በጀት ዓመት የትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን የሚጠናቀቅበት፣ በዕቅድ ክንውን ዘመኑ ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ሰፊ ተግባራት የተከናወኑበት በመሆኑ ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል በዓሉ ቃል የሚገባበት እንደሆነ

ተናግረዋል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እንዲህ ዓይነት በዓላት ላይ ሕዝቡን ሥራ በማስፈታት ልማት፣ ሠላም፤ ዴሞክራሲ፤ ሕገመንግስታዊ ሥርዓት  በሚሉ ኀሳቦች ደጋግሞ በማንሳትና ራሱን ይበልጥ አማራጭ የለሽ ፓርቲ አድርጎ የሚያቀርብበት በተቃራኒው ደግሞ የሚቀናቀኑትን ኃይሎች

ደግሞ ሽብር ናፋቂዎችና ጸረሰላም ኃይሎች በማድረግ ፕሮፖጋንዳ የሚሰራበት በአል ነው በማለት አስተያየታቸውን የተጠየቁ ወገኖች መመለሳቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።

«ባንዲራ ጨርቅ ነው» በማለቱ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞና ቁጣ ተቀስቅሶበት የቆየው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በአደባባይ ለሰራው ስህተት ሕዝቡን ይቅርታ ሳይጠይቅ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሚል ማክበሩ ሲያስተቸው ቆይቷል። መንግስት ከምርጫ 97 በሁዋላ የባንዲራ፣

የብሄር ብሄረሰቦች፣ የመከላከያ ቀኖች እያለ በመቶ ሚሊዮኖች የሞቆጠር ገንዘብ በማውጣት ያከብራል።