መንግስት ዘወትር አርብ የሚደረገው የተቃውሞ ስብሰባ እንዲቆም በጥብቅ አዘዘ

የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአወሊያ በተሰባሰቡ ሙስሊሞች የተመረጡ 17 የኮሚቴ አባላት የካቲት 26 ቀን 2012 ዓም ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ተክለማርያም በአወልያ እስከ ዛሬ ሲካሄድ የነበረው አይነት ተቃውሞ ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይካሄድ፣ ቢካሄድ ሀላፊዎቹ ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።

አቶ ሽፈራው የአወሊያ ተቃውሞ እንዲቆም ያዘዙት፣ ተቃውሞው ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ሀይሎች ሊጠቀሙበት መፈለጋቸውን መንግስት ተጨባጭ መረጃ ደርሶታል በሚል ምክንያት ነው። በውጭ አገር የሚኖሩ ጸረ ሰላም ሀይሎች ያሉዋቸውን ሚኒስትሩ በስም አልጠቀሱም።

መንግስት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያቀረባቸውን ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄዎች በቀጥታ ከመመለስ ተወካዮችን በማስፈራራት ተቃውሞውን ለማፈን መዘጋጀቱ ታውቋል። መንግስት ተወካዮቹ ላቀረቡት ጥያቄ በቂ መልስ ሰጥቻለሁ እያለ ቢሆንም ተወካዮቹ ግን መንግስት ጥያቄያቸውን በቀጥታ ከመመለስ ማስፈራራትን መርጧል ይላሉ።

የመንግስት ባለስልጣናት ተወካዮቹ ለህዝቡ “ጥያቀዎች ተመልሰዋልና ከእንግዲህ ተቃውሞ ማድረግ አያስፈለግም” ብለው እንዲነግሩ ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ነው።

ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት የሙስሊሙ ተወካዮች ከመንግስት በሚደርስባቸው ማስፈራሪያ ተንበርክከው ህዝቡ ተቃውሞ ከማድረግ እንዲቆጠብ ያድርጉት፣ ወይስ ህዝቡን ለተጨማሪ ተቃውሞ ያነሳሱት ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

ይሁን እንጅ ጉዳዩን በቅርበት እየተካከተለ የሚገኘው ዘጋቢያችን እንደሚለው ሙስሊሙ ተቃውሞውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያሳስቡ ወረቀቶች እየተሰራጩ ነው።

ወረቀቶችን ማን ያሰራጫቸው ባይታወቅም፣ አንዳንድ ወረቆቶች ሙስሊሙ ጥያቄውን ወደ ፊት እንዲገፋ፣ ካስፈለገም ከአንዋር መስጊድ ውጭ እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው።

ከዘገባያችን ለመረዳት እንደታቸለው በሙስሊሙ እና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ወደ የትኛውም አቅጣጫ ለመወሰድ ኳሱ ያለው በተወካዮቹ ላይ ነው። ተወካዮቹ ከዚህ ቀደም “መንግስት ጥያቄያችንን በተገቢው መንገድ ካልመለሰ ፣ በሂደት መወሰድ ስላለበት እርምጃ ህዝቡ እንዲወስን እናደርጋለን” ብለው መናገራቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide