(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2011) በሕዝብ መካከል ተሰግስገው ግጭቶችና ትንኮሳዎች በየአካባቢው ለማቀጣጠል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ አንዳንድ አካላት መንግስት ወደ ማይፈለገው ወታደራዊ ርምጃ እየገፋፉት ነው ሲል የጠቅላይ ሚኒስቲሩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ትላንት የት ነበርን ዛሬስ ወዴት እየሄድን ነው በሚል ርዕስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ባስተላለፈው መልዕክት እዚህም እዚያም ከለውጡ ጋር አብረው የማይሄዱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው ብሏል።
እነዚህ ጊዜያዊ ችግሮች ግን የለውጡን ሂደት አቅጣጫውን ማስቀየር አይችሉም ሲል ተናግሯል።
የለውጥ ሂደቱ መታየት ያለበት በዕለትና በአንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን በረዥም የጊዜ አውድ ውስጥ ጭምር እንደሆነ መንግሥት ያምናል፡፡
ትላንት ከሕገ-መንግሥት በሚቃረኑ አዋጆችና ደንቦች ከለላነት በዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረው ግፍ ምን ያህል ሰብዓዊ ጥፋት እንዳስከተለ የለውጥ ሂደቱ አደባባይ አውጥቷቸዋል ይላል በመልዕክቱ።
ትላንት የተፈጸሙ ወንጀሎችንና ጥፋቶችን እንደየሁኔታው በሕግ አግባብ የሚስተናገደውን በሕግ አግባብ እያስተናገደ ሲሆን ለይቅርታ የሚመጥኑት በደሎችና ስህተቶችም በልባዊ ይቅርታ ይስተናገዳሉ ብሏል ፡፡
ይህ የለውጥ ሂደት በቁርጠኝነት ተጀምሯል፤ ነገም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በርግጥ እዚህም እዚያም ከለውጡ ጋር አብረው የማይሄዱ ጊዜያዊ ክስትርቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ የለውጡ ሂደት ግን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡
ነገር ግን የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ ቀን ከሌሊት ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው በሚፈጥሩት ጦርነት፤ ሁከትና የኢኮኖሚ አሻጥር ምክንያት ሰላማዊና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ በማድረጋቸው የሚፈጠር ጊዜያዊ ሁኔታዎች ይታያሉ።
መንግሥት ሁሉንም ሰላማዊና ሕጋዊ አማራጮች ሁሉ አሟጦ ከተጠቀመ በኋላ በቂና ተመጣጣኝ አስተዳደራዊ፤ ሕጋዊና ወታደራዊ ርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና ይህንንም አጠናክሮ የሚቀጥልበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባም ብሏል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የወጣው መልዕክት።