ጥር ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በ2005 ዓም መንግስት 40 በ 60 በሚል ላወጣው መርሃ ግብር ከ163 ሺ በላይ ህዝብ የተመዘገበ ቢሆንም፣ እስካሁን ቤቶችን ሰርቶ ለማስረከብ አልቻለም። በፕሮግራሙ መሰረት 40 በመቶውን ቤት ፈላጊዎች ሲከፍሉ፣ ቀሪው 60 በመቶ በባንክ ብድር ይሸፈንላቸዋል።
ሆኖም መቶ በመቶ ለከፈሉ ቅድሚያ ይሰጣል በመባሉ ከ8 ሺ በላይ ነዋሪዎች የተጠየቁትን መቶ በመቶ ከፍለው ቤቱን ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
የአ/አ ከተማ አስተዳደር የቤት አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር ያልተጣጣመ ነው ያለ ሲሆን፣ የግንባታ እቃዎች ዋጋ ጨምሮአል በሚል ሰበብ ቀደም ሲል ለቤቶቹ ከሰጠው ዋጋ እጅግ የላቀ ዋጋ ለመጨመር መዘጋጀቱ ቤቶቹን እየተጠባበቁ ያሉ ወገኖችን አስደንግጦአል።
አስተዳደሩ ባለፈው አመት ሰኔ ወር 1 ሺ 200 ቤቶችን አስተላልፋለሁ በሚል ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ከስድስት ወራት ተጨማሪ ጊዜ በላይ ይህንንም አነስተኛ ቁጥር ማስረከብ አለመቻሉን፣ በዚህም ምክንያት ከዘመድ አዝማድ ተበዳድረው ለቤቱ ከሁለት አመት በፊት ክፍያ የፈጸሙ ዜጎች ችግር ላይ መውደቃቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጹም ሰሚ አላገኙም።
አንድ ቤት ፈላጊ ስለጉዳዩ ለዘጋቢያችን አስተያየቱን ሲሰጥ ከሁለት አመት በፊት ቤቶቹ በ18 ወራት ተገንብተው ይተላለፋሉ በተባለው መሰረት መንግስትን በማመን 300ሺ ብር መክፈሉን ነገርግን ከ24 ወራት ቆይታ በሁዋላም የቤቶች ግንባታ መጓተቱን ሲሰማ እጅግ ማዘኑን ተናግሯል።የ40 በ60 ቤቶች መቼና እንዴት እንደሚተላለፉ በአ/ አ አስተዳደር በኩል ግልጽ የሆነ መረጃ አለመሰጠቱን የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በአስተዳደሩ ችግር ምክንያት ገንዘባቸውንም አስይዘው ለቤት ኪራይ መዳረጋቸው ተጨማሪ ጉዳት አስከትሎባቸዋል።