መንግስት ከፋ ዞን ቲፒ ወህኒ ቤትን በመስበር እስረኞችን ያስመለጡት ታጣቂዎችን በሽምግልና ካስገባ በኋላ ማሰሩ ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2009)

በደቡብ ኢትዮጵያ ከፋ ዞን የቴፒ ወህኒ ቤትን በመስበር እስረኞችን ያስመለጡትን ታጣቂዎች መንግስት በሽምግልና ካስገባቸው በኋላ ወደ ወህኒ እንደወረዳቸው የአካባቢው ምንጮች ገለጹ።

በከተማው ነዋሪ ላይ የሚፈጸመው ግፍና በደል መጠናከሩንም እነዚሁ ምንጮች አስታውቀዋል። 

ከሁለት አመት በፊት ሃሙስ ግንቦት 27/2007 ሌሊት በቴፒ ከተማ ወህኒ ቤት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከመቶ በላይ እስረኞችን በማስፈታትና መሳሪያ በመንጠቅ ተመልሰው ጫካ የገቡት ታጣቂዎች ቁጥራቸው ከ100 እስከ 150 እንደነበርም በወቅቱ ተዘግቧል። የህወሃት ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋናም ጥቃቱ መፈጸሙን በማረጋገጥ በወቅቱ ዘገባ ያቀረበ ሲሆን ሶስት ፖሊሶችም መገደላቸውን ገልጾ ነበር።

ወጣቶቹ ወህኒ ቤቱን ሰብረው እስረኞቹን ማስመለጣቸውን ተከትሎ እነርሱን በማሳደድ ለመያዝና ርምጃ ለመውሰድ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይህንንም ተከትሎ ያመጹትን ወጣቶች በማግባባት ለመመለስ የክልሉ የጸጥታ ሃይልና የሀገር ሽማግሌዎች ጥረት አድርገዋል። ወጣቶችም ጥያቄያቸው እንደሚመለስ ቃል ስለተገባላቸውና የሀገር ሽማግሌዎች አማላጅ ሆነው በመገኘታቸው መሳሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለዋል። ሆኖም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ እነዚህን ወጣቶችና የእንቅስቃሴ መሪዎች ወደ ወህኒ ከወሰዳቸው በኋላ በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ የማእከላዊ ምርመራ አዲስ አበባ ከተማ በመሰቃየት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

እነዚህ የቴፒን ወህኒ ቤት ጭምር በመስበር በአከባቢው ከፍተኛ ተጽእኖ የፈጠሩትና ለፌደራሉም መንግስት ስጋትን ሆነው የተገኙት እነዚህ ወጣቶች በጥቅምት ወር 2007 በክልሉ የጸጥታ ሃላፊ አንዱ በስልክ ሲያግባባቸው የተቀረጸው በወቅቱ ለኢሳት ደርሶት ነበር።

በዚህ መልክ በማግባባትና በሽምግልና የገቡት ወጣቶች አሁን በማእከላዊ ምርምራ በስቃይ ላይ ሲሆኑ ሸምጋዮቹ የሀገር ሽማግሌዎች በተወሰደው ርምጃ ምን አቋም እንደያዙ የታወቀ ነገር የለም።

ወጣቶቹ በአከባቢው ተሰሚና ተጽኖ ፈጣሪ በነበሩበት ወቅት መንግስት በህዝብ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ እጅግም እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች ወጣቶቹ ወደ ወህኒ ከተወሰዱ በኋላ አፈናው ተጠናክሯል ብለዋል።