መንግስት ከጋምቤላ ክልል ወደ ግማሽ የሚሆነውን፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ 1/5 ኛውን መሬት ሊሸጠው ነው

መጋቢት ፳፪ (ሃይ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ አገዛዝ የእርሻ መሬቶችን ለባለ ሀብቶች በሊዝ የመሸጡን ሂደት አቋርጣለሁ ባለ በሳምንቱ ፈጣን የመሬት ሽያጭ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ይፋ አደረገ።

እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ዘገባ ፤በተለይም በሱዳን አዋሳኝ በሆኑት በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች አንድ ሄክታር መሬት በአመት በ1ዶላር ከ15 ሣንቲም ሂሳብ እየተቸበቸበ የአካባቢው ነዋሪዎቹ ግን መላ ህይወታቸውን ከሚገፉበት ቀዬ በግዳጅ መፈናቀላቸው ከፍተኛ ውግዘት በማስከተሉ ነበር መንግስት የመሬት ሽያጭ ሂደቱን  እንደሚያቋርጥ ያስታወቀው።

“መሬት በሊዝ የመስጠቱን ሂደት አቋርጨ እስካሁን ለባለሀብቶች በተሰጡት መሬቶች ላይ እንዴት እየተሰራባቸው እንደሆነ እገመግማለሁ”  ነበር ያለው ከሳምንት በፊት መንግስት ባወጣው መግለጫ ።

ይሁንና መግለጫው በተሰጠ በሳምንቱ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች ተጨማሪ 100ሺህ ሄክታር መሬት ለኢንቨስተሮች ለመስጠት መፍቀዱን በግብርና ሚኒስትር የእርሻ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ቢሮ ዳይሬክተር  አቶ ኢሳያስ ከበደ  ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ፤መንግስት አሁን ከሚሰጠው 100 ሺህ ሄክታር መሬት በተጨማሪ በመጭዎቹ ጊዜያትም ባዶ መሬትን ብቻ ሳይሆን በመሬቱ ላይ አስፈላጊ ግንባታዎችን በማሟላት ለመሸጥ መሰናዳቱ አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩን ጠቅሶ ብሉምበርግ እንዳለው ፤‘በአዲሱ እቅድ መሰረት መንግስት መሬቱን መንጥሮ፣ የመስኖ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክና ንጹህ ውሃን የመሳሰሉ ነገሮችን አሟልቶ የመሬቱን ዋጋና ተጨማሪ ወጭዎቹን ጨምሮ ለባለ ሀብቶች ለመሸጥ ተዘጋጅቷል።’

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የመሬት ጥናት ኢንስቲቲዩት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤  በአለማችን ካሉት 5 ከፍተኛ የምግብ እርዳታ ተቀባዮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ባለፉት 4 ዓመታት ብቻ ሳኡዲ ስታርን ጨምሮ ለተለያዩ ኢንቨስተሮች 400ሺህ ሄክታር መሬት በርካሽ የሊዝ ዋጋ ሸጣለች።

መንግስት በአጠቃላይ ለመሸጥ ያቀደው 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነው።

የመንግስት እቅዶች እንደሚያመለክቱት ከአጠቃላይ የጋምቤላ ክልል ወደ ግማሽ የሚጠጋጋውን ማለትም 42 ከመቶ ያህሉን፤ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ 1/5ኛ የሚሆነውን መሬት በሊዝ ለመሸጥ ተዘጋጅቷል።

ይህ ማለት እስካሁን የተሸጡትን ሳይጨምር  981 ሺህ ሄክታር መሬት በቅርቡ ለሽያጭ ይቀርባል።

እስካሁን የተከናወነው የሽያጭ ዋጋ እንደሚያመለክተው ፤ ካራቶሪ የተባለው የህንድ ኩባንያ ለአንድ ሄክታር መሬት በኣመት እየከፈለ ያለው 1 ዶላር  ነው።

 ይህም በወቅቱ ምንዛሬ ሢሰላ፤ አንድ ሄክታር መሬት ለአመት በ 20 የኢትዮጵያ ብር ገደማ  ተሽጧል ማለት ነው።

 በዓመት የ አንድ ሄክታር መሬት ዋጋ የሆነው 20 የኢትዮጵያ ብር በወቅቱ ገበያ መሰረት፤ ሩብ ሊትር ዘይት ወይም አንድ ኪሎ ስኳር የመግዛት አቅም አለው።

ከዚህ ከመሬት ንጥቂያና ከግዳጅ ሰፈራ ጋር በተያያዘ በተለይ በጋምቤላ በተደጋጋሚ ግድያዎችና አመፆች መከሰታቸው ይታወሳል።

ውጥረቱ በ አስፈሪ ሁኔታ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ “ሳውዲ ስታር” የተባለው የሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲ ካምፓኒ የሩዝ እርሻውን ለማስፋፋት ተጨማሪ 290ሺህ መሬት በጋምቤላ አካባቢ ለመግዛት እንደሚፈልግ በይፋ አስታውቋል።

“የመሬት ሽያጩን ሂደት ማስፋፋቱ ፤መንግስት ‘የልማት እቅዴ’ በሚለው በዚሁ ፕሮግራሙ ምክንያት የደረሱትን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች በተመለከተ ተጠያቂ የሚሆንበትን ጊዜ ያፋጥነዋል።” ሲሉ የኦክላንድ ኢኒስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

“የዓለም አቀፍ ለጋሽ አገራትም ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡትን እርዳታ እንዲያቆሙ እየተደረገ ያለውን ግፊት ይህ ውሳኔ ያፋጥነዋል።” ሲሉ ተሟጋቹ አክለው ገልጸዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide