ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2009)
መንግስት ከአንድ የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ጋር በሽርክና ለመስራት የገባው ውል ትርፍ ሊያስገኝ ባለመቻሉ ፋብሪካው ለጨረታ ቀርቦ ገዢ ማጣቱ ተገለጠ።
ሳይጊን ዲማ የተሰኘው ይኸው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ከአምስት አመት በፊት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ወደምርት ቢገባም ፋብሪካው የታሰበውን ያህል ገቢ ሊያስገኝ አለመቻሉን በሃገር ቤት ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ለሃገሪቱ ከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ የነበረው ይኸው ግዙፍ ፋብሪካ ባለፈው አመት ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች 105 ሺ ዶላር ገቢ ብቻ ማግኘቱን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ አስነብቧል።
በሰበታ ከተማ የሚገኘውን ይህንኑ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ካለበት እዳ ለመታደግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፋብሪካውን በ625 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ ጨረታን በተደጋጋሚ ቢያወጣም ገዢ ማጣቱ ተመልክቷል።
መንግስት በዚሁ ፋብሪካ 60 በመቶ ድርሻን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ ከመንግስት የፋይናንስ ተቋማት ብድርን ወስዶ በ40 መቶ ድርሻ የነበረው የቱርኩ ፋብሪካ 574 ሚሊዮን ብር ከንግድ ባንክ ወስዶ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና ፋብሪካው ላለፉት አምስት አመታት በምርት ላይ ቢቆይም የታለመለትን ውጤት ባለማስገኘቱ መንግስት ከቱርኩ ተቋም ጋር የነበረው የሽርክና ድርሻ እንዲቋረጥ መወሰኑን መገናኛ ብዙሃን አነብበዋል።
ባለፈው ሳመንት ከመንግስት ወደ አንድ ብሊዮን ብር ብድር ወስዶ የነበረ ሌላ የቱርክ ኩባንያ ብድሩን ሳያወራርድ ከሃገር መውጣት መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ልማት እና ንግድ ባንኮች ለቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ከፍተኛ ብድርን ሲሰጡ ቢቆዩም ፋብሪካዎቹ ውጤት ሊያስመዘግቡ አለመቻላቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። የባለፈው አመት የሃገሪቱ የጨርቃ ጨርቅቅ ምርት ገቢ በ21 በመቶ አካባቢ መቀነስ ማስመዝገቡንም ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ አጥቶ የሚገኘውን ይህንኑ ፋብሪካ በምን ሁኔታ ማስተዳደር እንዳለበት የተለያዩ አማራጮችን እያየ እንደሚገኝም ታውቋል።