መንግስት እየወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ ተቃውሞን ከማባባስ ውጭ መፍትሄ አያመጣም ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 16 ፥2008)

የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እየወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ ህዝባዊ ተቃውሞውን ከማባባስ ውጭ መፍትሄ አያመጣም ሲሉ የኦባማ አስተዳደር የዲሞክራሲና የሰብዓዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለስልጣን የገለጹት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ቀጣዩ ብሄራዊ ስራ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጸጥታ፣ ብልጽግናና ስኬት አሜሪካንን በቀጥታ ይመለከታል ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና የስራ ረዳት ሃላፊ ቶም ማሊኖውስኪ፣ ሆኖም በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው ቀውስ ሁለቱ አገራት ሊፈጽሙ ባቀዱት ግብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ባሰራጩት ጽሁፍ ገልጸዋል።

ሃላፊው በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተከስቱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ለኢትዮጵያና ለአሜሪካ ከፍተኛ ፈተና እንደሆኑ ቶም ማሊኖውስኪ ባሰራጩት ጹሁፍ ገልጸው፣ በህገመንግስቱ የተገለጹ የአስተዳደርና ችግርና የፖለቲካ ብዝሃነት ማነስ ላይ ተመስርተው የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው ሲሉ በጹሁፋቸው አብራርተዋል። ኢትዮጵያውያን በመንግስት ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልጉ የገለጹት ቶም ማሊኖውስኪ፣ ህዝባዊ ተቃውሞን የገለጸው ህዝብ በህገመንግስቱ የሰፈሩትን መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቁ መሆኑን ገልጸዋል።

“አሜሪካ ፍጹም አገር አይደለችም፣ የህዝብን ብሶት በተመለከተ  ትምህርት ወስደናል ያሉት ማሊኖውስኪ ኢትዮጵያ አሁን በውስጣዊ ችግሮች ተወጥራለች፣ እናም የሰላምና አንድነቷ ከፍተኛ አድጋ ተጋርጦባታል በማለት አክለው ገልጸዋል።

ሚስተር ማሊኖውስኪ አሁን በአማራና በኦሮሚያ የተከሰተውን ህዝባዊ ተቃውሞ በተመለከተ ሲገልጹ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአካባቢያቸውና በህይወታቸው ጉዳይ ያገባናል ብለው ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ፣ የውጭ ጠላቶች ስራ ነው ብሎ ቸላ ማለት የለበትም ብለዋል።

የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያሉት ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ መቆም እንዳለበት፣ ግድያ እንዲቆም፣ የታሰሩ እንዲፈቱ፣ እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡትም እንዲቀርቡ ምክር የሰጡት የኦባማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን፣ የህዝብን ጥያቄ በሃይል ለመቀልበስ መሞከር ችግሩን ከማባባስ ውጭ ሌላ ለውጥ አያመጣም ብለዋል።

የፖለቲካ መሪዎችን ማሰርና የሲቪል ማህበረሰብን ማገድ፣ ህዝባዊ ንቅናቄውን አያቆመውም ያለው የቶም ማልዌንስኪ ጽሁፍ፣ መንግስት ከማን ጋር ስለሰላም እንኳን መደራደር እንዳለበት ምንም ክፍተት አይሰጥም ሲል ገልጿል።

የኢንተርንነት መዘጋት፣ ተቃውሞውን አያረግበውም ያለው የቶም ማሊኖውስኪ ሃተታ፣ ድርጊቱ ይልቁንም የውጭ ኢንቨስተሮችንና ቱሪስቶች ላይ ፍርሃት ያሳድርባቸዋል ብሏል። ለጊዜውን አመጹን ለማስቆም ሃይል መጠቀም የባሰ ንዴትና ቁጭት ከመፍጠር ውጪ አመጹን አያስቆመውም ሲል ደምድሟል።