መንግስት አዲሱን የፕሬስ ካውንስል በበላይነት ለመምራት እየሰራ ነው

ሚያዚያ  ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ እያካሄደ ካለው ሪፎርም ስራ ጋር
በተያያዘ ለመወያየት ስብሰባ ቢጠራም፣ መንግስት በቀጥታ በማይመለከተው የፕሬስ ካውንስል ምስረታ አጀንዳ ላይ
ሲመክር ውሎአል።
ባለፈው ዕረቡ በሒልተን ሆቴል በተጠራው ስብሰባ ላይ የኢትዮጽያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት በሚል የሚታወቀውን
የፕሬስ ካውንሰል በሚመሰረትበት ጉዳይ ላይ የመንግስትና የግል የሚዲያ ባለቤቶችና ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበትና
አቶ ሽመልስ ከማል የመሩት ይህው የአንድ ቀን ስብሰባ፣  ዋንኛ ትኩረቱ የነበረው የመንግስትና የግል
መገናኛ ብዙሃንን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ምክክር ማድረግ እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

የዛሚ ኤፍኤም ራዲዮ ባለቤት ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ በአስተባባሪነት የሚመሩት በምስረታ ሒደት ላይ ይገኛል የተባለው
ይህው የመገናኛ ብዙሃን ም/ቤት እውን ለማድረግ ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀ ጥረት ሲደረግ የቆየ ሲሆን እነ ወ/ሮ
ሚሚ በምንና እንዴት እንደተመረጡ በማይታወቅ ሁኔታ የመስራች ኮምቴ ሰብሳቢ ሆነው የመቀመጣቸው ነገር በሚዲያ
ተቋማትና ባለቤቶች ዘንድ እስካሁን ድረስ መደናገርን ከመፍጠር ባሻገር ጥርጣሬና ቅሬታንም እያስከተለ ጉዳይ
የምስረታውን ሒደት አጓቶታል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደተናገሩት የካውንስሉ ምሰረታ ሒደት የግል ጋዜጦች ዘውትር በሚያንጓጥጡትና
በጎ አመለካከት በሌላቸው በእነወ/ሮ ሚሚ በመያዙ የዘርፉን ተዋንያን ተገቢውን ድጋፍ ከመነፈጋቸው ጋር ተያይዞ
የምስረታ ጉባዔ ለማካሄድ እንዳልተቻለ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል ከ10 ዓመታት በፊት መንግስት የፕሬስ ካውንስልን ራሱ ለማቋቋም አሁን በስራ ላይ ባለው
የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ሕግ ውስጥ አካትቶት እንደነበረና ነገር ግን ካውንስሉ በመንግስት ከሚቋቋም
ነጻ ሆኖ በዘርፉ ተዋንያን ቢቋቋም የተሻለ ይሆናል በሚል የቀረበውን ኀሳብ መቀበሉን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን
ከዛሬ ነገ የዘርፉ ተዋንያን ካውንስሉን ይመሰርታሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከሚገባው በላይ ምስረታው የመጓተቱ ጉዳይ
መንግስትንም እንዳሳሰበው ጠቁመዋል፡፡
በወ/ሮ ሚሚና ምንም አባላት በሌሉት በመንግስት አምሳል በተፈጠረው ኢጋማ በተባለው ማኀበር የሚመራው ጊዜያዊ ኮሚቴ ግን ካውንስሉን ለመመስረት የተለያዩ ቅድመዝግጅቶች መደረጋቸውን፣ካውንስሉ የመንግስትና የግሉን ሚዲያ አጣምሮ በመያዝ በአቅም ግንባታ እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እንደሚያይ በመጥቀስ የካውንስሉ ቋሚ ገቢ ምን ይሁን በሚለው ጉዳይ
ላይና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ እንዳላገኙ ሪፖርት አድርጓል፡፡

በስብሰባው ላይ ጣልቃ ገብነት በማይኖርበት ሁኔታ ፓርላማ በየዓመቱ ለካውንስሉ በጀት ቢመድብለት የሚል ኀሳብ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን አንዳንድ ወገኖች ወጪው በአባላት መዋጮ ቢሸፈን ይሻላል የሚል ኀሳብ አቅርበዋል፡፡
መንግስት በሚዲያ ካውንስል ምስረታ እጄ የለበትም ቢልም በእነወ/ሮ ሚሚ በኩል ካውንስሉን ለመቆጣጠር አስቦ
እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመጥቀስ በምስረታ ላይ ያለው ካውንሰል በመንግሰት ታግቷል በሚል ጋዜጠኞች
ከወዲሁ ቅሬታቸውን እያቀረቡ መሆኑ የምስረታው ጉዳይ ላይ የራሱን ጥላ አሳርፏል፡፡
የኮምኒኬሽን መ/ቤቱ በፕሬስ ካውንስል ላይ ቢወያይም ስብሰባው በዚህ ጉዳይ ያለምንም መቋጫ መበተኑ ታውቋል፡፡
መንግስት በአንድ በኩል በፕሬስ ካውንሰል ምስረታ ውስጥ አያገባኝም እያለ በሌላ በኩል ካውንስሉ ካልተመሰረተ
በሚል በጋዜጠኞች ላይ እየፈጠረ ያለው ቀጥተኛ ጫና እርስበርሱ የሚጋጭ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪ ጋዜጠኞች ተችተውታል፡፡

ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን በመገደብ በአለም በግንባር ቀደምነት ስማቸው  ከሚጠቀሱ አገራት መካከል ትመደባለች።