ሐምሌ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- መንግስት አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት መኖራቸውን የድምጽ ወይም የቪዲዮ ምስል አቅርቦ ማሳየት እንዳለበት ኢሳት አሳሰበ::
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢዲቶሪያል ቦርድ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ዛሬ አቶ በረከት ስምኦን ኢሳት ላቀረበው ዜና የሰጡትን መልስ በማስመልከት ነው።
አቶ በረከት ሪፖርተርና ሰንደቅ ለተባሉት ጋዜጦች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኢሳትን ዜና በማስተባበል መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ በረከት ኢሳትን በማስመልከት ሲናገሩ ” እነዚህ ሀይሎች የሀሰት ወሬ በሀገራችን ላይ ሲያሰራጩ ዛሬ የመጀመሪያቸው አይደለም። በተለይም በሰሜን አፍሪካ ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ ትርምስ ተከትሎ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው እውነታ ውጪ ፣ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ስራቸው አድርገውት ከርመዋል። የእነዚህ ሀይሎች አላማ አንድ እና አንድ ብቻ ሲሆን ፣ ይሀውም ያልተጫበጠ መረጃ በማሰራጨት ህብረተሰቡን ወደ ትርምስ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው። ይህ ከሰሜን አፍሪካ የፖለቲካ ቅጥያ የትርምስ ስትራቴጂያቸው አልሰራ ስላላቸው በአዲስ መልክና ስልት አሁን መምጣታቸው ይሆናል።” ብለዋል።
አቶ በረከት በሪፓርት ጋዜጣ ላይ ለማንኛውም አሉባልታ መግለጫ አንሰጥም በማለት ከተናገሩ በሁዋላ ነው፣ ዛሬ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት።
የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ሁለት አመታት እውቅና ላለመስጠት በመፈለግ ኢሳት ለሚያቀርባቸው ዘገባዎች መልስ ሰጥቶ አለማወቁን፣ ከ2 አመታት በሁዋላ ተገደው ለኢሳት እውቅና መስጠታቸውን እንደሚያሳይ ቦርዱ ጠቅሷል።
ቦርዱ አክሎም፣ ከዚህ ቀደም የኤርትራው ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና የዝምባብዌ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሮበርት ሙጋቤ ሞተዋል የሚል ዜና በአለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን ሳይቀር ሲተላለፍ፣ ሁለቱም መሪዎች ወደ አደባባይ በመውጣት በሙሉ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ማሳየታቸውን አስታውሷል። ኮሚኒስት አገር በምትባለዋ ኩባ እንኳን የጓድ ፊደል ካስትሮ የጤና ሁኔታ ለህዝቡ በየጊዜው ይፋ ይደረግ ነበር ያለው ቦርዱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ገዢው መታመማቸውን እንኳ አምኖ የተቀበለው ዜናው በኢሳት እና በሌሎች አለማቀፍ መገናኛ ብዘሀን ከወጣ በሁዋላ ነው ብሎአል። ይህም መንግስት የሚመራውን ህዝብ ምን ያክል እንደሚንቀውና ምን ያክል በጨለማ ውስጥ አኑሮ ሊገዛው እንደሚፈልግ ያሳያል ብሎአል።
የኢሳት ኢዲቶሪያል ቦርድ የኢትዮጵያ መንግስት አንድ ጊዜ በቃል አቀባዩ፣ ሌላ ጊዜ በአምባሳደሮች፣ ደስ ሲለው ደግሞ ስልጣን ለቀዋል በተባሉ ሰዎች የተምታታ መግለጫ ከሚያስነግር ይልቅ ፣ ህዝቡን ለማረጋጋትም ሆነ የኢሳትን ዜና ለማስተባበል አቶ መለስ ዜናዊን በአካል አቅርቦ ለህዝብ እንዲያሳይ፣ ይህን ማድረግ እስካልቻለ ጊዜ ድረስ በተደጋጋሚ መግለጫዎች በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ትርምስም ሆነ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስቆም አይቻልም ብሎአል።
አቶ በረከት ኢሳት ዜናው ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርግ የቅንብር ስራ አልሰራም ብለው ከመውቀስ፣ እጅግ ቀላሉ መንገድ ” ይሀው መሪያችን” ብሎ ማሳየት ነው ያለው ኢሳት፣ አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ በተለይም ለራሱ ደጋፊዎች ሲል አቶ መለስን አቅርቦ በቴሌቪዥን እንዲያሳይ ጠይቋል።
እነ አቶ በረከት እንደሚሉት ሳይሆን፣ ኢሳት ለኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት የገባውን ቃል መቼውንም ጊዜ ቢሆን እንደማያጥፍ የገለጠው ቦርዱ፣ አቶ ሽመልስ ከማል ኢሳት የአቶ መለስን መታመም ይፋ ሲያደርግ ይህ የኢሳት ወሬ ነው በማለት የገለጡትን በማስታወስ፣ ውሸትን በመናገር ” የውሸት መታወቂያ” የተሰጠው አካል ማን እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል ብሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢሳት ድረገጽ የተቋረጠው ከዜናው ጋር በተያያዘ ነው በማለት ሪፖርተር ጋዜጣ የዘገበው ምኞቱን ነው በማለት ቦርዱ አጣጥሎታል። በመላው አለም የሚገኙ ጎብኝዎች የኢሳትን ድረገጽ በአንድ ጊዜ በመጎብኘት የመስመር መጨነናነቅ መፍጠራቸውንና አገልግሎቱን የሚሰጠው ድርጅት የጎብኝዎች ቁጥር ከስምምነቱ በላይ በመሄዱ ስርጭቱ የተቋረጠ መሆኑን ያስታወቀው ኢዲቶሪያል ቦርዱ፣ ችግሩን በመቅረፍም በ24 ሰአት ውስጥ ለመመለስ ተችሎአል ብሎአል።
ኢሳት የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት በተመለከተ መረጃውን በአለማቀፍ የአደጋ ተንታኝ በእንግሊዘኛው አጠራር ICG ውስጥ ከሚሰሩ ታማኝ ምንጮች ማግኘቱን መግለጡ ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የህወሀት አባላት የአቶ መለስ የጤንነት ሁኔታ እንዲነገራቸው ግፊት መጀመራቸው ታውቓል። በርካታ የድርጅቱ ከፍተኛ ካድሬዎች፣ በህዝቡ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት እየጨመረ በመሄዱ ውድባችን ወይም ድርጅታችን እውነታውን ያስታውቀን በማለት ለነባር ታጋዮች ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረው ግራ መጋባት አመራሩ መልስ ለመስጠት እየከበደው መምጣቱን የኢሳት የውስጥ ምንጮች ይናገራሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide