ጥቅምት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዘጋቢያችን እንደገለጠው በመላ አገሪቱ የሚገኙ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከገቢያቸው ጋር ያልተመታጠነ ግብር እንዲከፍሉ በመገደዳቸው ከመማረር አልፈው የንግድ ድርጅቶቻቸውን እየዘጉ፣ የቻሉትም ስደትን እየመረጡ ነው ።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነጋዴ እንደተናገሩት ሁለት ክፍል ቤታቸውን በወር 800 ብር በማከራየት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ቢሆንም ከ2 ሺህ ብር በላይ የሆነ የአመት ግብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው፣ የሚይዙትን አጥተዋል።
አንዲት ሌላ እናት ደግሞ በወር 1 ሺ ብር ቤት አከራይተው ቢኖርም ውዝፍ ግብር እንዲከፍሉ በመደረጋቸው ለመክፈል መቸገራቸውን ተናግረዋል
በሆቴል አገልግሎት ዙሪያ የተሰማሩ ነጋዴዎችም በጥናት እና በመረጃ ያልተደገፈ ግብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው ምሬታቸውን እየገለጡ ነው።
መንግስት የጀመራቸውን ሰፋፊ የልማት ስራዎች ለማስጨረስ ሲል ከፍተኛ ግብር ለማስከፈል መገደዱን ይናገራል።
ምሁራን በበኩላቸው ግብር የጨመረበት ዋነኛ ምክንያት መንግስት ከገቢው ጋር ያልተጣጣመ ከአቅሙ በላይ የሆኑ የልማት እቅዶችን በመዘርጋቱ እንዲሁም በስለላ እና በደህንነት ስራ ላይ በርካታ ሰዎች በመቀጠራቸው የእነሱን ደሞዝ ለመሸፈን ሲባል ነው በማለት ይከራከራሉ።
አይኤም ኤፍ በነጋዴው ላይ የሚጣለው ግብር ኢኮኖሚውን ሊጎዳው እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቅ መቆየቱ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ዜናም የመንግስት ሰራተኞች እንደገና የአቶ መለስን ራእይ ለማሳካት በሚል የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲለግሱ እየተገደዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት ባለበት በዚህ ጊዜ የወር ደሞዛችንን በአመት እንድንከፍል መገደዳችን ህይወታችንን መሪር አድርጎታል ይላሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግስት ሰራተኞች።