ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2008)
መንግስት በጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በደረቅ ወደብ ከአንድ ወር በላይ የቆዩ ንብረቶችን ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ እንደሚወርስ ማሳወቁ ከአስመጪ ነጋዴዎች በኩል ተቃውሞን ቀሰቀሰ።
በተያዘው አመት በሞጆ ደረቅ ወደብ ከተከማቹት ወደ 12ሺ ኮንቴይነሮች መካከል ወደ 1ሺ የሚገመቱ ከሁለት ወር በላይ ጊዜን ያስቆጠሩ እንደሆነ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታውቋል።
እነዚሁ በደረቅ ወደብ የተከማቹ ንብረቶች እሰከ ግንቦት 1 ድረስ ካልተነሱም መንግስት ንብረቶቹን እንደሚወርስ ባለስልጣኑ ገልጿል።
ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች ንብረታቸውን መውሰድ ያልቻሉ አስመጪ ነጋዴዎች መንግስት የሰጠው ማሳሰቢያ አግባብ አለመሆኑን በማስታወቅ ተቃውሞን ማቅረብ መጀመራቸው ታውቋል።
አስመጪ ነጋዴዎች ኮንቴይነሮቹን በጊዜ ያልወሰዱት ከብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ወረፋ ስለሚጠብቁ እንዲሁም የፋይናንስ ችግር አጋጥሟቸው ስለሚገኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግስት ተወካዮች ምክክርን ያደረጉት ባለሃብቶች ንብረታቸው መቼ ወደ ሃገር ውስጥ እንደገባ መረጃ በወቅቱ እንደማይደርሳቸው እንዲሁም ብድርን ከባንኮች ስለማያገኙ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።
መንግስት በዘርፉ ያሉ በርካታ ችግሮችን ሳይመለከት ንብረቶቹን ከሶስት ቀን በኋላ እወርሳለሁ ማለቱ አግባብ አይደለም ሲሉ እነዚሁ አስመጪዎች አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ በደረቅ ወደብ ያሉ ንብረቶች ባለመነሳታቸው ሳቢያ በጎረቤት ጅቡቲ ወደብ መጨናነቅ ተፈጥሯል ሲሉ ለባለሃብቶቹ ምላሽን ሰጥተዋል።