መንግስት በዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ላይ ከፍተኛ ክትትል እያደረገባቸው ነው ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2008)

ከወራት በፊት ከእስር የተፈቱት የዞን ዘጠኝ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን አባላት ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከሃገር እንዳይወጡና በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፈተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸው መሆኑን አስታወቁ።

በቀድሞ ስራቸው ላይ መሰማራት እንዳልቻሉ የሚናገሩት አባላቱ ዳግም ወደ እስር ቤት ልንገባ እንችላለን የሚል ስጋትም አድሮባቸው እንደሚገኝ መግለጻቸውን ቪኦኤ እንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል።

የተመሰረተባቸው የሽብርተኛ ክስ ተቋርጦ ከአምስት ወር በፊት ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ፓስፖርታቸው በፀጥታ ሃይሎች ተይዞባቸው መቆየቱንም አስረድተዋል።

በእስር ቤት ቆይታው በደረሰበት በደል አንደኛ ጆሮ እንደማይሰራ ያስታወቀው ጦማሪ አቤል ዋበላ የአባላቱ የእለት ከእለት ቁጥጥር እየተደረገባቸውና የመንቀሳቀስ መብታቸውም ተነፍጎ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከእስር ከተፈታን በኋላ በከሳሽ አቃቤ ህግ የቀረበብንን ይግባኝ እንደሰንሰለት (እስር) ነው የምንመለከተው ያለው ሌላኛው ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔ ዳግም እስር ቤት እገባለሁ የሚል ስጋት አድሮበት እንደሚገኝ አስታውቋል።

ከተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የሰላ ትችት የሚቀርብበት የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞቹንና ጦማሪያኑ በውጭ ሃገር ካሉ ሃይሎች ጋር በመተባበር ህገ-መንግስቱን ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል ሲል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ይሁንና አሜሪካንን ጨምሮ ከበርካታ ወገኖች የቀረበን ተቃውሞ ተከትሎ የፍትህ ሚኒስቴር በተከሳሾቹ ላይ የተመሰረተውን ክስ በማቋረጥ ከእስር መልቀቁ ይታወሳል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ በበኩሉ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ መፈታት የለባቸውም በማለት ውሳኔውን ተቃውሞ ይግባኝ አቅርቡ የሚገኝ ሲሆን፣ የዞን ዘጠኝ አባላቱም በይግባኙ ሳቢያ ፍርሃት አድሮባቸው መቆየቱን አስረድተዋል።

መቀመጫውን በዚሁ በአሜሪካ ያደረገውን በጋዜጠኞች መብት መከበር ዙሪያ የሚሰራው Committee to Protest Journalism (CPJ) በበኩሉ የዞን ዘጠኝ አባላቱ ዳግም ወደ እስር ቤት መግባት ተቀባይነት የሌለውና ለሃገሪቱ የነጻ ሚዲያና ነጻነት አደጋ መሆኑን ገልጿል።