ኢሳት ((ሃምሌ 12 ፥ 2008)
መብታቸውን በጠየቁ የወልቃይት ተወላጆች ላይ የተወሰደውን ዕርምጃ እንደሚያወግዝ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ዓለም አቀፍ ቡድን አስታወቀ።
የኦፌኮ አለም አቀፍ የድጋፍ ቡድን ሃምሌ 10 ፥ 2008 ባወጣው መግለጫ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ለመብቱ የሚያደርገውን ትግል እንዲያቀናጅም ጥሪ አቅርቧል።
“በጎንደር የተወሰደው የሃይል ዕርምጃ እና የተከሰተውን ቀውስ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫ” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ “የማንነት ጥያቄ ይሁን ሌላ የመብት ጥያቄ መንግስት በህጋዊና ህገመንግስታዊ አኳሃን መፍታት ሲገባው ራሱ ህግና ህገመንግስቱን እየጣሰ ሃገሪቱን ለቀውስ ዳርጓታል” በማለት ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ተጠያቂ አድርጓል።
“የኦሮሞ አብዮት በተቀሰቀሰበት 8ኛ ወር ሃምሌ 4 ፥ 2008 ጎንደር ላይ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል” በማለት ክስተቱን ያስተላለፈውና በሃገሪቱ ቀውስ መቀጠሉን ያመለከተው የኦፌኮ አለም አቀፍ ቡድን፣ መብቱን በጠየቀ ህዝብ ላይ የሚወሰደውን ህገወጥ የሃይል ዕርምጃ እናወግዛለን በህዝብ ላይ የሚደርሰውን የሃይል ዕርምጃና እስራት እንዲያቆም አጥብቀን እንጠይቃለን።” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ለእስራት የተዳረጉ የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል። ባለፉት 8 ወራት የተገደሉና የተጎዱ ዜጎትንም በተመለከተም በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ጠይቋል።
በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ የትግልና የትብብር ጥሪ አቅርቧል።
“ለ25 አመታት በህዝባችን ላይ የተንሰራፋው ፋሺስታዊ አገዛዝ አሽቀንጥረን ለመጣል በጋራ ታግለን ነጻነታችንን ከማስከበር ውጭ አማራጭ የለንም ስለዚህ መላው የአገራችን ህዝብ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ህጋዊና ሰላማዊ ትግል እንዲያቀናጅ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲል መግለጫው ቋጭቷል።