ጥር 1 ቀን 2004 ዓም
ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በነ በቀለ ገርባ በሽብርተኝነት ወንጀል በከሰሳቸው ዘጠኝ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ከቦረና ሞያሌ እና ከሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ዞን ያስመጣቸውን አባላቱ አዲስ አበባ ሆቴል አስቀምጦ የምስክርነት ቃል በማስጠናት ዋና የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ያላቸውን 18 ሰዎች ትላንትና እና ዛሬ በዋለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት አቀርቧል፡፡
የተቀሩ ሰባት የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን፣ የሰነድ ማስረጃዎችንና በኤግዚቢትነት ከተከሳሾች ያዝኳቸው ያላቸውን ቁሳቁሶች ለማቅረብ ፍርድ ቤቱ ለጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ፍርድ ቤት ሲጠይቃቸው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር መሆናቸውን ገልጸው በግሌ የኦሮሞ ህዝብ በኢህአዴግ መንግሥት የተገፋና የተጨቆነ ነው ብዬ ስለማምን በሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ተሳትፌ በመታገሌና መንግሥት የደበቀውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለአምንስቲ ኢንተርናሽናል በማጋለጤ ነው የታሰርኩት ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ (ኦህኮ) ፓርቲ ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ በበኩላቸው “እኔ ሙሉ ጊዜዬን በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማሳልፍ ሰው ነኝ፣ የታሰርኩትም ለአምንስቲ ኢንተርናሽናል የሀገር ገጽታ የሚያበላሽ የሰባዊ መብት ጥሰትና የድርቅ መረጃ ሰጠህ ተብዬ ነው” ሲሉ፣ ፍርድ ቤቱ ወንጀል ሰርቻለሁ ወይም አልሰራሁም የሚለውን ብቻ አስረዱ እንዲህ ዓይነት ነገር ለመስማት ይሄ ፍርድ ቤት አልተሰየምም ብሎ አስቁሟቸዋል፡፡
ሌሎች 7 ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠይቃቸው በ2002 ዓም ከኦነግ ለመንግሥት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጥተው መመለሳቸውን ጠቅሰው ምንም ወንጀል ሳንሰራ ነው በሚያውቁን ሰዎች እያስጠቆሙብን የያዙን ብለዋል፡፡
የዐቃቤ- ሕግ የመጀመሪያ ምስክር አቶ ጌትነት ተካ የኦህኮ ፓርቲ ኋላፊ የሆኑት የአቶ ኦልባና የመኖሪያ ቤቱ ሲፈተሸ በኦሮምኛ ቋንቋ የተጻፉ ሠነዶች፣ ሲዲዎች፣ የኦሮሞ የቦረና ባህል ልብስ ሆኖ ኮፍያው ላይ የኦነግ አርማ ያለበት ልብስ ለብሶ የተነሳውን ፎቶ መመልከቱን መስክሯል፡፡
ነገር ግን የተከሳሽ ጠበቃ ባነሱት መስቀለኛ ጥያቄ የኦነግን አርማ ከዚህ ቀደም እንደማያውቅ ገልፆ፣ ኦሮምኛ ቋንቋ መስማትም ሆነ ማንበብ እንደማይችልና ተገኙ የተባሉትን ሰነዶች ይዘታቸውን አለማወቁን ለፍርድ ቤቱ በመንገር ፖሊሶች የኦነግ አርማና የኦነግ ሰነድ መሆኑን እንደነገሩት ገልጻል፡፡
የዐቃቤ- ሕግ ሦስተኛ ምስክር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የገላን ትምህርት ቤት መምህር መሆኑን ለፍርድ ቤቱ የገለጸው አቶ ኢዮሲያስ አበራ፣ የኦፌዴን ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በክረምት የመምህራን ትምህርት አጥንቶ የመመረቂያ ጽሑፉን ሲሰራ የእርሱ አማካሪ እንደነበሩና አንድ ቀን ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ቢሯቸው ስንገባ የኢህአዴግ መንግሥት ኦሮሞን፣ ሶማሌንና የደቡብ ህዝቦችን አጥብቆ ስለሚጠላ በ2004 ዓ.ም በየትምህርት ቤታችን ማስተማር ስንጀምር አመጽ በማነሳሳት መንግሥትን እንድናወርድ አወያይተውናል ብሎ መስክሯል፡፡
አቶ በቀለ ገርባ በዚህ ፍርድ ቤት እኔ መብት ካለኝና እውነቱ እንዲወጣ ከተፈለገ ምስክሩን ራሴ መስቀለኛ ጥያቄ እንድጠይቀው ፍርድ ቤቱ ይፍቀድልኝ ብለው ቢጠይቁም የግራ ዳኛው ጠበቃዎት ውክልናቸውን ካነሱና በግልዎ የሚከራከሩ ከሆነ ብቻ ነው የሚፈቀድልዎት በማለት ውድቅ አድረገውባቸዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቃ ምስክሩን “ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን አብራችሁ ለማውራት እንዴት ቻላችሁ የውይይት ክበብ ነበራችሁ?” ብለው ሲጠይቁት ፣´” የለም በአንድ ቀን ግንኙነት ብቻ ነው ኦሮምኛ ከሚችሉ ሁለት ጓደኞቼ ጋር ያወሩን ወሬውንም የጀመሩት እርሳቸው ናቸው በሰበታ የመሬት ዝርፊያ ላይ አርቲክል እጽፋለሁ ብለው” በማለት መልሷል፡፡
ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸው ሌሎች ምስክሮች በአብዛኛው የመሰከሩት ከ 3ተኛ እስከ 9ነኛ ባሉ ተከሳሾች ላይ ነበር፡፡