መንግስት በእስራኤል አገር የሰለጠኑ የደህንነት ሀይሎችን አሰማራ

ሰኔ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ የብሄራዊ ጸጥታና  ደህንነት መስሪያ ቤት በእስራኤል አገር በታል አራድ ኔጊቭ ማሰልጠኛ ጣቢያ ያሰለጠናቸው  987 የደህንነት ሰራተኞች በመላ አገሪቱ በሚገኙ 572 ታላላቅ መስጊዶች እና በቴሌኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት ማሰማራቱን ከደህንነት መስሪያ ቤት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል ፡፡

ከሰልጣኞች መካከል 11 ዱ ብቻ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ አረብኛ  አቀላጥፈው የሚናገሩ ፣ ቁራንን በስርዓት የተማሩ እና እስልምናን ስርዓቶች ሙሉ በሙሉ የሚፈጽሙ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ ሰልጣኞች በቴሌ ኮሚኒኬሸን መስሪያ ቤት የተመደቡ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ በስልክ ጠለፋ  ስራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ ከሰልጣኞች መካከል 631 ዱ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ሲሆኑ፣ በትምህርት ደረጃም የ2002 ምሩቃን በብዛት ይገኙበታል።

በቴሌ የተቀጠሩት አዲሶቹ የደህንነት ሰራተኞች መንግስት ከፈቀደላቸው ውጭ ሌላ የስልክ ግንኙነት የተጠቀሙትን ሚኒስትሮች በድምጽ እንዲለዩ በተሰጣቸው ፈተና መሰረት የተወሰኑ ሚኒስትሮችን ስም ዘርዝረው አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ከሰተ ብርሃን አድማሱ፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ሙክታር ከድር፣ የንግድ ሚኒስትርነት አቶ ከበደ ጫኔ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደርና ሪፎርም ዘርፍ (ክላስተር) አስተባባሪ  አቶ ሙክታር ከድር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ፣እንዲሁም  የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል መንግስት ከፈቀደላቸው የስልክ ግንኙነት ውጭ በራሳቸው መንገድ ስልክ ሲያወሩ ተገኝተዋል ።

ባለስልጣኖቹ በእነዚህ ስልኮች ተጠቅመው የተናገሩት በ ዶ/ር ደብረ ጽዩን አማካኝነት ወደ መረጃ እና ደህንነት ቢሮ መተላለፉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኢሳት መንግስት በእስራኤል አገር ልኮ ያሰለጠናቸውን የደህንነት ሰራተኞች እውነተኛ ስም እና ዝርዝር ታሪክ አስፈላጊ ነው ብሎ በሚያምንበት ጊዜ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ለማስታወቅ ይወዳል፡፡