ጥር ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በያዝነው ፈረንጆች አመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ለርሃብ የተጋለጠ መሆኑ እየታወቀ በመንግስት በኩል ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተደርጎ የሚሰጠው መግለጫ በለጋሽ አገራት ዘንድ ብዥታ መፍጠሩን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተናግረዋል።
ስማቸው እንደይገለጽ የገለጹ የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንዳሉት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የሚሊዮኖችን ህይወት አደጋ ላይ መጣሉ በገሃድ እየታየ ቢሆንም፣ መንግስት ችግሩን አደባባይ በማውጣት በማሳወቅ እርዳታ ፈጥኖ የሚደርስበትን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ፣ ችግሩ በቁጥጥር ስር ውሎአል፣ በቂ እርዳታ አለ በሚል የሚሰጠው መግለጫ፣ በለጋሽ አገራት ዘንድ ብዥታን ፈጥሮአል።
ለጋሽ አገራት እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ቢሆኑም፣ መንግስት ከአለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የእርዳታ ጥያቄው አፋጣኝ መልስ እንዲያገኝ ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ስምምነት የተደረገባቸውን ነጥቦች ሳይቀር በመጣስ በመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ሁሉም ነገር የተስተካከለ እንደሆነ የሚሰጠው መግለጫ፣ ብዥታን እየፈጠረ ነው። ባለፉት 10 አመታት ስለኢትዮጵያ የተነገረው አወንታዊ ዜና፣ ለጋሽ አገራት ኢትዮጵያ በራሱዋ ችግሩን ትወጣዋለች የሚል እምነት እንዲያሳድሩ እንዳደረጋቸውና ለጋሽ አገራቱን ማሳመን ቀላል ስራ አለመሆኑን በማወቅ መንግስት አደጋውን በግልጽ በመናገርና የውጭ የመገናኛ ብዙሃን ገብተው እንዲዘግቡ በማድረግ እርዳታ የሚገኝበትን መንገድ እንዲያፈላልግ መክረዋል።
አሁን የተያዘው አቋም የ15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥለው ይሆናል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በድርቁ ሳቢያ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ትምህርት ማቋረጣቸው ታውቋል። አብዛኞቹ ተማሪዎች በውሃ እጥረት ሳቢያ ለማቋረጥ መገደዳቸውንና ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ መምህራን ትምህርት ቤቶችን ዘግተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል።