መንግስት በምእራብ አርሲ ዞን የተገደሉትን ሙስሊሞች ቁጥር መቀነሱን የአካባቢው ሰዎች ገለጹ

ሐምሌ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምእራብ አርሲ ዞን በኮፈሌና አካባቢዋ የፌደራል ፖሊሶች በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ በወሰዱት እርምጃ 3 ሰዎች መገደላቸውና 7 ሰዎች መቁሰላቸውን የኦሮምያን ፖሊስ በመጥቀስ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ቢዘግቡም የኢሳት ምንጮች በበኩላቸው የሟቾች ቁጥር ከ18 እስከ 25 ይደርሳል ይላሉ።

በአካባቢው የሚገኝ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሟቾችን ቁጥር 18 መሆኑን ሲገልጽ፣ ወደ ኮፈሌ እና ዋቢ ከተሞች ለመግባት ሙከራ አድርጎ በፖሊሶች ፍተሻ ተንገላቶ ሳይሳካለት የቀረው ዘጋቢያችን ከከተሞች ሲወጡ ያገኛቸውን ሰዎች አነጋግሮ እንዘገበው የሟቾች ቁጥር ከ15 እስከ 20 ሊደርስ እንደሚችል ገልጿል።

መንግስት ሙስሊሞቹ የጦር መሳሪያዎችን እንደያዙ አድርጎ ያቀረበው ዘገባ ትክክል አለመሆኑና የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ለግድያው ተጠያቂዎች መሆኑን የአካባቢውን ሰዎች አስተያየት በማሰባሰብ ዘጋቢያችን ገልጿል።

በዛሬው እለትም ውጥረት ሰፍኖ መዋሉንና ምናልባትም ለሁለተኛ ጊዜ ግጭት ሊከሰት እንደሚችል አክሎ ተናግሯል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ፖሊሶች የኮፈሌ ጎረቤት ከተሞች ወደ ሆኑት አሳሳ ፣ ዶዶላና ኮሬ አምርተዋል። ከፍተኛ ውጥረት በሚታይበት ቢዘህ አካባቢ ግጭት ከተነሳ በቀላሉ ላይበርድ እንደሚችል ዛሬ ከሰአት በሁዋላ ወደ አካባቢው የተጓዘው ዘጋቢያችን ገልጿል።

በሙስሊም ወገኖች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም እያወገዙት ነው። በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የህወሀት ኢህአዴግ የፌደራል ፖሊስ አባላት የሀይማኖት መሪዎቻቸው ወይም ኢማሞቻቸው መታሰራቸውን በተቃወሙ ዜጎች ላይ የፌዴራል ፖሊሶች በከፈቱት ተኩስ  25ቱን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩትን  ማቁሰላቸውን ገልጾ፣ ድርጊቱን በጽኑ ኮንኗል።

ህወሀት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የኦሮሞን ህዝብ በተለይም የአርሲ ኦሮሞዎችን ኢላማ ማድረጉን የገለጸው ኦነግ ፣ በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚፈጸመው የሽብር ጥቃት ህወሀት ህዝቡን የማፅዳት አጀንዳ እንዳለው የሚያሳይ ነው ብሎአል።

ህወሀት የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስተዳደር የሞራል ብቃት የሌለው መሆኑን የገለጸው ኦነግ፣ ህዝቡ  ባገኘው መሳሪያ ሁሉ ራሱን እንዲከላከልና አገዛዙን ለማስወገድ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

ግንቦት7 “ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ወያኔን እናስወግድ!!” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ “በወያኔ ፋሽስታዊ እርምጃ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻች” የተሰማው መሪር ሀዘን ገልጿል።

“ወያኔ በሥልጣን መንበር ላይ ውሎ ባደረ መጠን እንዲህ ዓይነቱ መርዶ  መስማታችን የማይቀር ነው ” የሚለው ግንቦት7፣ገዳዮች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸውም ገልጿል።

በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን እና መሠረታዊ  መብቶቻችን ተከብረውልን መኖር እንድንችል ወያኔን ለማስወገድ ህዝቡ ቆርጦ እንዲነሳም ግንቦት 7 ጠይቋል።

መንግስት የድምጻችን ይሰማ አባላትን በሙሉ አሸባሪ ብሎ እንደሚፈርጃቸው ይገልጻል።