ኀዳር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ መንግስት በአንድ በኩል የውጭ እርዳታ እየጠየቀ በሌላ በኩል ረሃቡን ብቻውን እንደሚቋቋመው መግለጹ ግራ እያጋባ ነው።
የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ችግሩ ከመንግስት አቅም በላይ አይደለም ብለዋል። በሌላ በኩል ግን መንግስት ላቀረበው የእርዳታ ጥሪ አለማቀፉ ማህበረሰብ በበቂ ሁኔታ መልስ አልሰጠም በሚል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅሬታ እያቀረበ ነው። አለማቀፉ ማህበረሰብ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከ270 ሚሊዮን ዶላር እንዲለግስ ድርጅቱ አሳስቧል።
ሚኒስትሩ ዛሬ መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የድርቁን ችግር ለመመከት መንግስት በራሱ አቅም ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን፣ ችግሩ ከመንግስት አቅም በላይ ባለመሆኑ እስካሁን ባለው ግምገማ ከሕዝብ ወይንም ከባለሃብቶች ዕርዳታ ለማሰባሰብ አለመታሰቡን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ከችግሩ ጋር ተይያዞ የጀመራቸውን የልማት ፕሮጀክቶች እንዲያጥፍ አስገዳጅ ሁኔታ እንዳልገጠመው ጠቅሰው፣ በቀጣይ አስገዳጅ ሁኔታ ከገጠመ ፕሮጀክቶችን የማዘግየት ሁኔታ ለኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ይሁን እንጅ ኢሳት ቀድም ብሎ እንደዘገበው የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና የጤና ተቋማት ግንባታቸው በዚህ አመት እንደማይጀመር ተነግሯቸዋል።
ሚኒስትሩ ከድርቁ ጋርም ተያይዞ አንድም የሞተ ሰው አለመኖሩን በመጥቀስ የቢቢሲን ዘገባ ቅጥፈት ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
ይህንኑ ለማስረገጥ ይመስላል የመንግስት ጋዜጠኞች በረሃብ ምክንያት ልጇን ያጣችውን ወ/ሮ ብርቱካን አሊን ልጄ የሞተው በበሽታ ነው ብለሽ ተናገሪ በማለት እንድታስተባበል ለማድረግ ሞክረዋል።ወ/ሮ ብርቱካን ግን በጫና ውስጥ ሆኗ እንኳን የቀሪዎቼ ልጆች ህይወት ያሳስበኛል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ሳትገልጽ አላለፈችም አለማቀፍ ድርጅቶች 15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መራባቸውንና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሁንም እየገለጹ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ግብረሃይል ዛሬ ባወጣው ሪፖርት 1 ሚሊዮን 370 ሺ በርሃብ የተጠቁ ወገኖችን ለመርዳት ከሶስት ቀናት በፊት 17 ሚሊዮን ዶላር መለገሱን ገልጿል። እስከ ፊታችን ታህሳስ ወር መጨረሻ 8 ሚሊዮን 200 ሺ ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚሹ፣ ከጥር ወር በሁዋላ የተረጅው ቁጥር በሁለት እጥፍ እንደሚጨምር አስታውቋል። መንግስት፣ ለጋሽ አገራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ የሚያደርጉት ጥናት በሚቀጥለው ወር ይፋ ሲሆን፣ ትክክለኛው የተረጅ ቁጥር እንደሚታወቅ የገለጸው ድርጅቱ፣ ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ምግብ ለማቅረብ 270 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሷል። እስካሁን ድረስ የአለማቀፉ ማህበረሰብ 120 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል። አለማቀፉ ማህበረሰብ ለተጎጂ ቤተሰቦች ምግብ እያቀረበ ባለበት ወቅት፣ መንግስት ብቻውን ምግብ እያቀረበ እንዳለ አድርጎ መናገሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳምንታዊ ዘገባ ጋር የሚጋጭ ሆኗል።
የተለያዩ ኢትዮጵያውያን አደጋው አለማቀፍና አገራቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ሰፊ ዘመቻ ጀምረዋል።