መንግስት ሙስሊሙን ለመከፋፈል ከፍተኛ ሩጫ ላይ ነው

ሐምሌ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአወልያ የተጀመረው የሙስሊሙ እንቅስቃሴ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ መንግስት አንዳንዱን በግድ ሌላውን በመደለል በእየ ክፍለሀገሩ የሚገኙ ሙስሊሞችን ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን እንዲያወግዙ እያደረገ ነው። አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የሙስሊም መሪ ለአዲስ አበባው ወኪላችን እንደገለጡት፣ መንግስት በ1997 ዓም ቅንጅትን ከፋፍሎ  ለመምታት የተጠቀመብትን ዘዴ በሙስሊሙ ላይ ተግባራዊ እያደረገ ነው።

በየክፍለሀገሩ የሚገኙ ሙስሊሞች የአወልያውን እንቅስቃሴ እንዲያወግዙ እየተገደዱ መሆኑንም እኝሁ ሰው ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተፈጠረውን ችግር ለማብረድ ሙከራ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ችግሩን የሚያባብስና ወደ ግጭት የሚያመራ ውሳኔ በትናንትናው እለት አሳልፎአል።

መጅሊሱ መጪው የጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ በቀበሌ መካሄድ ይገባዋል በማለት የመንግስትን አቋም እንደወረደ ተቀብሎ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በዋጣው የአቋም መግለጫ ላይ ” ማህበረሰብ በአወናባጆች ሳይደናገር የምክር ቤቱን ውሳኔዎች እየተከተለ እንዲጓዝ ፤ የዋህብያና ሰለፊያ አክራሪ እምነት አራማጆች በአሁኑ ወቅት የሰደቃና የአንድነት ኮንፍረንስ እያሉ የሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች ከእምነቱ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ሃራም ነው” ሲል ገልጧል።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒሰትር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም “ባለፈው አርብ መዲናችን አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን በምታካሂድበት ወቅት አክራሪ ሃይሎች ሆን ብለው ከተማዋን ለማተራመስ ያደረጉት ጥረት ዓላማቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው” ብለዋል።

“አንዳንድ አክራሪ ሃይሎች የእስልምና እምነትን ተገን በማድረግና የሰደቃ ድግስና የአንድነት ኮንፍረንስ በማዘጋጀት እኩለ ሌሊት ላይ ነዋሪዎችን ለሁከትና ትርምስ በመቀስቀስ በ19ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ወቅት ከተማዋን ለማተራመስ አቅደው ነበር ” ብለዋል።

መጅሊሱ ያወጣውን መግለጫ እንዲሁም መንግስት በአወልያ በተገኙ ሙስሊሞች ላይ የወሰደውን እርምጃ ለመቃወም ፣ ህዝበ ሙስሊሙ በአንዋር መስጊድ በብዛት እንዲወጣ የሚያሳስቡ ጥሪዎች በሞባይል ስልኮች  እየተላለፉ ነው።

መንግስት የአቶ መለስ ቁርጥ ታውቆ አንድ ውሳኔ እስኪወሰን ድረስ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ እርምጃ አይወስድም የሚል እምነት እንዳላቸው ዘጋቢያችን የነጋገራቸው የሙስሊሙ መሪ ተናግረዋል። “መንግስት መሪዎችን ማሰር ቢፈልግ ኖሮ እስካሁን አይታገስም ነበር” የሚሉት እኝሁ መሪ፣ ከአቶ መለስ ህለፈተ-ህይወት ወይም ከስራ- መወገድ ጋር ተያይዞ በአገሪቱ የተፈጠረው ውጥረት በሙስሊሙ ላይ በሚወሰድ እርምጃ ተባብሶ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ ” አይፈልጉም ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide