መንግስት ለአባይ ግድብ ግንባታ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለማሰባሰብ የነበረው እቅድ ችግር እንዳጋጠመው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 25 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመገንባት ባለው የአባይ ግድብ ግንባታ በተለይ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ለማሰባሰብ የነበረው እቅድ ችግር እንዳጋጠመው ገለጸ። 6.5 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካ መንግስት ለመክፈልና የተመሰረተበትን ክስ ለማቋረጥ መወሰኑንም አስታውቋል።

ባለፈው አመት ሰኔ ወር የአሜሪካው ሴኪውሪቴስ ኤንድ ኤክስቼንጅ (American Securities and Exchange Commission) ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካን ህግ በጣሰ መልኩ የቦንድ ሽያጭ አካሄዷል ሲል የቦንድ ሽያጭ እንዲቋረጥ በማድረግ በመንግስት ላይ ክስ መስርቶ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና የክስ ሂደቱ መጀመርን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት 6.5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያን ለመክፈል በመስማማት ክሱ ዕልባት እንዲያገኝ አድርጓል።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2014 ድረስ መንግስት ባካሄደው ህገወጥ የቦንድ ሽያጭ 3100 አካባቢ ኢትዮጵያውያን 5.8 ሚሊዮን ዶላር ሊሰበሰብ ተችሎ እንደነበር የአሜሪካውን ኮሚሽን በወቅቱ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።

ይኸው የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ በተደረጉ ጥረቶች ላይ ችግር ፈጥሮ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ የግድቡን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። በተለይ በአሜሪካ ከሃገሪቱ የቦንድ ሽያጭ አሰራር ጋር በተገናኘ በተፈጠረው ችግር የገንዘብ ድጋፍ ተቋርጧል ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

መንግስት ለግድቡ ግንባታ በውጭ ሃገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለማሰባሰብ ካቀደው የቦንድ ሽያጭና ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘውን ከዚህ ከአሜሪካ ለማግኘት እቅድ ነድፎ እንደነበርና ሰፊ ዘመቻ ሲያካሄድ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና የአሜሪካው ሲኪሪቴስ ኣንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን (American Securities and Exchange Commision) የኢትዮጵያ መንግስት የቦንድ ሽያጩን ለሚመለከተው አካል ካለማሳወቁ በተጨማሪ ድርጊቱ የአሜሪካንን ህግ የጣሰ ተግባር ነው ሲል በክሱ ገልጾ እንደነበር ከድርጊቱ ለመረዳት ተችሏል።

መንግስት ለአራት አመት ያህል የሰበሰበውን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ እንዲመልስ ከመደረጉ በተጨማሪ ከ600ሺ ዶላር በላይ ወለድ እንዲከፈል መደረጉም አይዘነጋም።

ባሳለፍነው ዕሁድ የአባይ ግድብ ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል በተከበረ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካው የቦንድ ሽያጭ እንዲቋረጥ በመደረጉ በገንዘብ ማሰባሰቡ እቅድ ላይ እክል ማስከተሉን አስታውቋል።

ይሁንና በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች የተለያዩ ዝግጅቶችን በማካሄድ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት እንደሚደረግ የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አክለው ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት አመታት በውጭ ሃገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ36 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰባሰቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ከ3 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ሚኒስትሩ አክሎ ገልጿል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው ወደ ሃገር የሚልኩት ገንዘብ ከሃገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ እየበለጠ መምጣቱን የብሄራዊ ባንክ ሲገልፅ ቆይቷል።