ኢሳት (ሃምሌ 14 ፥ 2008)
በቅርቡ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ የሚደርስ የመንገድ ፕሮጄክት ተሰጥቶት የነበረ አንድ የህንድ ስራ ተቋራጭ ኩባንያ የተረከበውን ስራ ሳያጠናቅቅ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ ከሃገር ኮበለለ።
በዚሁ ፕሮጄክት ስር ይሰሩ የነበሩ ከ200 በላይ ሰራተኞች ሊከፈላቸው የሚገባ የአንድ ወር ከግማሽ ደሞዝ ሳይከፈላቸው መቅረቱን በመግለጽ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የ958 ሚሊዮን ብር የመንገድ ፕሮጄክት ተሰጥቶት ስራውን ሳያጠናቅቅ የተሰወረው ኩባንያ ከሃገር ይዞ የወጣውን ገንዘብ ለማስመለስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
ኤስ ኢ ደብሊው (S.E.W) የተሰኘው ኩባንያ ከሶስት አመት በፊት 66 ኪሜ ርዝመት ያለው ከሃዋሳ ጭኮ የሚደርስ መንገድ እንዲሰራ ውል ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ መንገዱ በተያዘው ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና፣ በስራው ላይ ከፍተኛ መጓተት ታይቶበታል የተባለው ኩባንያው እስካሁን ድረስ 22 ኪሎሜርት ብቻ እንደሰራ የመንገዶች ባለስልጣን ድርጅት ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
ድርጅቱ የ958 ሚሊዮን ብር ፕሮጄክት ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ በሶስት አመት ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰደ የተገለጸ ነገር የለም።
የህንዱ ኩባንያ በአጠቃላይ የተሰጠው ገንዘብ ከመግለፅ ተቆጥቦ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ ድርጅቱ በስሩ ለሚሰሩ ሃገር በቀል ድርጅቶች መክፈል የነበረበትን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ከሃገር ይዞ መውጣቱን ይፋ አድርጓል።
ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር ስራውን ሲሰራ የቆየው የህንዱ ኩባንያ ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሮጄክቱ አጓትቷል ተብሎ የተሰጠው ኮንትራትን እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንንና፣ የኮንትራቱ መቋረጥን ተከትሎ የኩባንያው ሃላፊዎች ገንዘቡን ይዘው ከሃገር እንደወጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ኩባንያው በአጠቃላይ ስለተከፈለው ገንዘብ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ከወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በጋምቤላ ክልል በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ የህንድ ባለሃብቶች የተረከቡትን ብድር ሳያወራርዱ ከሃገር መኮብለላቸውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
በርካታ የህንድ ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት በስኳር ፋብሪካ እና በመንገዶች እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።