መብራት ሀይል በምዝበራና በብልሹ አሰራር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማባከኑን ጸረ ሙስና ኮሚሽን በጥናት አረጋገጠ

መስከረም ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጸረ ሙስና ኮሚሽን  በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውስጥ ስላለው የንብረት አስተዳደር አሰራር ስርዓት ጥናት አካሒዶ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት መገኘቱን አረጋግጧል።

በጥናቱ የተለየው የመጀመሪያው ችግር እቃዎች ተገዝተው ወደ ንብረት ክፍል ከመግባታቸው በፊት ንብረት ክፍሉን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደረግ የሚያስችለውና ወጥነት ያለው የማሳወቂያ ስርዓት አለመሰራት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ግዥዎች ከተፈጸሙ በኋላ ለእቃ ግምጃ ቤቶች ወጥነት ባለው እና እቃዎችን በተሟላ ሁኔታ የሚገልፁ የሰነድ ኮፒዎች በወቅቱ ወይም ቀድመው አይደርሷቸውም።

ንብረት ክፍሎች ያለበቂ የመረካከቢያ ሰነድ በጥድፊያ ንብረቶችን እንዲረከቡ መጠየቃቸው  ለተጨማሪ ወጪዎች መዳረጉ፤ እቃዎቹ ተገቢ ባልሆነ ቦታ እዲቀመጡና ለብልሽት እንዲጋለጡ እንዲሁም የጥራት ችግር ያለባቸው እቃዎች እንዲገቡ እንደሚደረግ ጥናቱ አመልክቷል፡፡

በጥናቱ ከ 150 ሚልዮን ብር በላይ በሰነድ ማጭበርበር ሙስና ተፈጽሟል። ተገዝተው የሚገቡ እቃዎች ትክክለኛነት የሚረጋገጥበት (የጥራት ቁጥጥር) ስርዓት ወጥነት የሌለው ፣ቀልጣፋ ያልሆነ እና አስተማማኝነት የጎደለው መሆኑ ሌላው ችግር ሆኖ ተጠቅሷል።

በተቋማቱ ታቅደው የሚገዙ እቃዎችን ለስራው በሚፈለጉበት ደረጃ እና በተጠየቁበት ስፔስፊኬሽን መሰረት ስለመገዛታቸው በሚመለከታቸው ሙያተኞች በአስተማማኝ ሁኔታ ሳይረጋገጡ እንዲሁም ማረጋገጫው ለሚመለከታቸው እና ለንብረት ክፍሎች በወቅቱ እንዳይደርሳቸው በማድረግ በዚሁ መሰረት የገቢ ሰነድ እየተሰራላቸው ገቢ አለመደረጋቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በዚህም በሁለት የበጀት አመታት የአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢልዮን ብር ውድመት መድረሱ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንም ከ45 በላይ የሚሆኑት ግዥዎች ገቢ ከተደረጉና ክፍያ ከተፈፀመባቸው በኋላ ስራ ላይ ሲውሉ ችግሮች ያጋጠሙበት ሁኔታ ታይቷል።

ከ45 ሺ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ፒኖች የቴክኒክ ችግር ያለባቸውና ከአምስት አመት በላይ ስራ ላይ ሳይውሉ ተቀምጠው ተገኝተዋል፤ ሌሎች እቃዎች ደግሞ ከተገዙበት ሀገር ሲመጡ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው በኮርፖሬቱ ግቢ ውስጥ በአቅራቢው ድርጅት ቀለም እየተቀቡ አዲስ የማስመሰል ስራዎች እየተከናወነባቸው መሆኑን የፌደራል የስነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሺን መርማሪዎች መረጃ አረጋግጦዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውስጥ ተገዝተው የሚመጡ የመለዋወጫ እቃዎች በንብረት ክፍል በአደራ መረከቢያ ቅፅ ተመዝግበው የገቢ ሰነድ ሳይሰራላቸው ከ 3-6 ወራት የሚቆዩ በመሆናቸው እቃዎቹ ችግር ቢኖርባቸው እንኳን በወቅቱ ለማስመለስ የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

እንዲህ አይነት ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ የአሰራር ክፍተቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ቢያረጋግጥም በአሰራር ችግሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ መቸገሩን አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንም በተመሳሳይ ሁኔታ ችግሮች የሚታዩ ሲሆን በተለይ እቃዎች ተገዝተው ሲመጡ በምን አይነት ቦታዎች ላይ እና በምን ያህል መጠን ተደርድረው መቀመጥ እንደሚገባቸው፣ ከፀሃይና ዝናብ እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያሳይ ማንዋል ከእቃዎቹ ጋር እንደሌለና የእቃ ግምጃ ቤት ሰራተኞች በትክክል እንደማያውቁት፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው የተገዙ ንብረቶች በየሜዳው ላይ ተበታትነው በሳርና በቅጠላቅጠሎች የተሸፈኑ በመሆናቸው የእሳት አደጋ ቢፈጠር ከፍተኛ ውድመት ሊደርስባቸው በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ለምዝበራ መጋለጣችውም ተጠቁሟል፡፡

በጥናቱ ችግር ሆኖ የተገኘው ሌላው ጉዳይ የገቢ ሠነድ ሳይሰራላቸው በስቶር ውስጥ በክምችት የሚገኙ እቃዎች መኖራቸው ነው፡፡ ከዚሁ  ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንም በእቃ ግምጃ ቤት ያሉ ንብረቶች ስራ ላይ ሳይውሉ ተጨማሪ ግዥዎችን በማከናወን አላስፈላጊ ክምችት የተፈጠረበት ሁኔታ ታይቷል፡፡

በጥናቱ በርካታ ችግሮች ተዘርዝረው ቀርበዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት ለሁለት አመታት በህንዶች እንዲመራ መንግስት መወሰኑ ይታወቃል።