መስፍን ኢንጂነሪንግ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በአዲስ አበባ አስመረቀ

ኢሳት (ታህሳስ 11 ፥ 2009)

የህወሃት ንብረት የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ የፔጆ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ማስመረቁ ተነገረ።

በያዝነው የፈረንጆች አመት ተመሳሳይ የፔጆ መገጣጠሚያ በትግራይ ክልል ያስመረቀው መስፍን ኢንጂነሪግን አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ሌላ የማስፋፊያ ፋብሪካ አስመርቋል።

በአዲስ አበባ የተገነባው ይሄው የመስፍን ኢንጂነሪንግ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በአመት እስከ 1 ሺ 200 መኪኖች እንደሚያመርት የህወሃት አገዛዝ ደጋፊ የሆነ ድረገጽ ዘግቧል።

መኪና የመገጣጠም ስራን በፋና-ወጊነት ይዘው ሆላንድ ካር በሚል በኢትዮጵያ ስራ የጀመሩት ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ በመንግስት ተፅዕኖ እንዲከሰሩ ተድርገው ከሃገር መውጣታቸው ይታወሳል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በትግራይና በአዲስ አበባ ሁለት የፔጆ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች የገነባው መስፍን ኢንጂነሪንግ ምርቱን ወደ ጅቡቲና ሶማሊያ ለመሸጥ ማቀዱ ተነግሯል።

መስፍን ኢንጂነሪግን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ወስዶ የተበላሸ በሚል ገንዘቡን ሳይመልስ መቅረቱ መዘገቡ ይታወሳል።

መስፍን ኢንጂነሪግን ከህወሃት የኤፈርት ንብረቶች አንዱ ሲሆን፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስና የመንግስት ጨረታዎችን በመውሰድ ልዩ ጥቅም የሚያገኝ ድርጅት ነው።