(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 29/2010) በአማራ ክልል መሳሪያ ለማስፈታት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታወቀ።
በሶስት ምዕራፎች በተከፈለ አሰራር በክልሉ መሳሪያ የታጠቁትን በሙሉ ለማስፈታት የሚያስችል ዝርዝር መመሪያ ነገ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይም በጎጃምና በሰሜን ጎንደር መሳሪያ ማስፈታቱ ትኩረት የተሰጠባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ታውቋል።
ማታለያና መደለያ ከማቅረብ አንስቶ በተለያዩ ዘዴዎች መሳሪያ ለመንጠቅ በአገዛዙ በኩል የሚከፈተውን ዘመቻ ለማክሸፍ ህብረተሰቡ ዝግጁ ሆኖ እንዲጠብቅ ጥሪ ተደርጓል።
አሁን በስልጣን ላይ የሌሉት የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱ ዘውትር የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ የአማራው ህዝብ መሳሪያ መታጠቁ ነው። በየጊዜው በሚደረጉ የሁለቱ ድርጅቶች ስብሰባ ላይ አቶ አባይ ወልዱ ሳያነሱ፡ ሳይጠቅሱ የማይልፉት ይሄንኑ የአማራው መሳሪያ የማስፈታት ጉዳይ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ለኢሳት ከሚልኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል። አቶ አባይ ወልዱ ይህን በሚሉበት ወቅት በሺዎች ለሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች መሳሪያ ማስታጠቁን ለአፍታም ዘንግተው አያውቁም ነበር። በእሳቸው እግር የተተኩት የአሁኑ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል የፌደራል መንግስቱ ባልስልጣን በነበሩ ጊዜ በተደጋጋሚ ሞክረዋል። በቀደመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ዋንኛ የኮማንድ ፖስቱ ተግባር የነበረው የአማራውን ህዝብ ትጥቅ ማስፈታት ቢሆንም ሊሳካ እንዳልቻለ በወቅቱ ተገልጿል።
ዶ/ር ደብረጺዮን አሁንም እጅ አልሰጡም። አማራውን መሳሪያ የሚፈታበትን መንገድ ቀይሰው፡ በሶስት ምዕራፎች ለማከናወን ተዘጋጅተዋል። ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው የአማራውን ህዝብ መሳሪያ ለማስፈታት በሶሶት ምዕራፎች የተከፈለ አሰራር ተዘጋጅቷል። በቅደም ተከተል ተፈጻሚ እንዲሆኑ በሚል የታቀዱት ሶስቱ ምዕራፎችን በተመለከተ በነገው ዕለት ዝርዝር መረጃው ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። በመጀመሪያው ምዕራፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ፡ በቀዬ መንደራቸው ተሰሚነታቸው ከፍ ያለ፡ በጀግንነት የሚታወቁ ሰዎችን በመለየት መሳሪያቸውን መንጠቅ እንደሚሆን ተገልጿል። በዚህም ሀብት ንብረት ያላቸው ሰዎችም መሳሪያ እንዲፈቱ ይደረጋል። በየሚኖሩበት አከባቢ በማህበረሰቡ ዘንድ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትም በመጀመሪያው ምዕራፍ መሳሪያቸውን የሚነጠቁ እንደሚሆን በዕቅድ ደረጃ ተይዟል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የሚከናወነው የመሳሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው መሳሪያ የታጠቁ የአማራ ክልል ነዋሪዎችን ትጥቅ ማስፈታት ነው። ይህኛው ምዕራፍ ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ዕቅዱን ያወጡት የአገዛዙ ሰዎች ከወዲሁ አስታውቀዋል። ህብረተሰቡ መሳሪያውን ለመፍታት ፍቃደኛ እንደማይሆን የተረዱት የአገዛዙ ባልስልጣናት በተለያዩ መደለያዎች ለመንጠቅ እንደታቀደ ተገልጿል። ጥቆማ ለሚያደርጉ ሰዎች መጠነኛ ማብረታቻ ገንዘብ እንደተዘጋጀም ታውቋል። በሶስተኛው ምዕራፍ መሳሪያ እንዲፈቱ የሚደረጉት በህጋዊ መንገድ የታጠቁት እንደሚሆኑም ተመልክቷል። በዚህኛው ምዕራፍ አብዛኞቹ በአገዛዙ እውቅና የተሰጣችው፡ አገልጋይነትና ታማኝነታቸው ተመዝኖ እምነት የተጣለባቸው እንደሆኑም ታውቋል። ሆኖም እነዚህኞቹም ለአገዛዙ ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን በመጥቀስ እየተለዩ ለተወሰኑት ብቻ ፍቃዱ እንዲቀጥል የሚደረግበት አሰራር ነው። በሶሶቱ ምዕራፎች በሚደረግ ዘመቻ ለአገዛዙ አደጋ ይፈጥራሉ ከሚባሉት የመሳሪያ ባለቤቶች ላይ ሙሉ በሙሉ የታጠቁትን መሳሪያ ለማስፈታት መታቀዱን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
ኢሳት ያነጋገራቸው አንዳንድ ነዋሪዎች እንደሚሉት አገዛዙ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳለ የሚያመላክት እርምጃ ነው። ካለፉት 6 ወራት ወዲህ በከፍተኛ መጠን የመሳሪያ ግዢ መፈጸሙንና በተለይ በአማራው ክልል የመሳሪያ ግዢ መጧጧፉን በአገዛዙ በተዘጋጀ የብሄራዊ ደህንነት ሰነድ ላይ መገለጹ የሚታወስ ነው። ህብረተሰቡ ከውዲሁ ጥንቃቄ በማድረግ በአገዛዙ የሚከፈተውን መሳሪያ የማስፈታት ዘመቻ እንዲያከሽፈውም ጥሪ ተደርጓል።