ግንቦት ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት (ህወሃት) ንብረት የሆነው መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ 200 የጭነት መኪኖችን ከውጭ ለማስመጣት 721 ሚሊዮን ብር በህገወጥ መንገድ ጠይቆ ፈቃድ ማግኘቱን የባንኩ ምንጮች ከላኩት የሰነድ ማስረጃ ለማረጋጋጥ ተችሏል።
መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው ህግ የጠየቀውን ገንዘብ ለመበደር እንደማያስችለው ካወቀ በሁዋላ የባንኩ የቦርድ አባላት በልዩ ሁኔታ ብድሩን እንዲፈቅዱለት ጠይቋል። ሰኔ 17፣ 1985 ዓም በ240 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መቀሌ ላይ የተቋቋመው የትምእት (ኢፈርት)ቅርንጫፍ ድርጅት የሆነው መሰቦ ስሚንቶ በ5 የአክሲዮን አባላት የተመሰረተ ነው። ህወሃት ከሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ ኩባንያው እንደገና በግል ካምፓኒ (private limited company) እንዲቋቋም ተደርጓል። በሰነዱ ላይ ለመመልከት እንደሚቻለው የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ወይም ባለቤቶች ትምእት (ኢፈርት) እና ህይወት እርሻ ሚካናይዜሽን ናቸው። ሁለቱም ኩባንያዎች የህወሃት ንብረት ሲሆኑ ፣ ህይወት እርሻ ሚካናይዤሽን በኢፈርት ስር ተመዝግቦ እያለ እንዴት በድጋሜ በመሰቦ ስሚንቶ ላይ የአክሲዮን ድርሻ ይዞ እንደተመዘገበ ግልጽ አይደለም። መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በአሁኑ ሰአት 740 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አለው።
ኩባንያው ከመስረታው እና ከማስፋፋት ስራው ጋር በተያያዘ እስከ 2007 ዓም ድረስ 3 ቢሊዮን 621 ሚሊዮን 945ሺ 17 ብር ከ66 ሳንቲም ከልማት ባንክ የተበደረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 2 ቢሊዮን 36 ሚሊዮን 531 ሺ 387 ብር ከ58 ሳንቲም የሚሆነውን እዳውን ሲከፍል፣ 1 ቢሊዮን 241 ሚሊዮን 288 ሺ 849 ብር ከ52 ሳንቲም ቀሪ እዳ እንዲሁም 795 ሚሊዮን 242 ሺ 537 ብር ከ82 ሳንቲም የወለዱ እዳ እንዳለበትና በድጋሜ ብድር በወሰደበት ወቅት 285 ሚሊዮን 661 ሺ 947 ብር ከዜሮ ሳንቲም አስቀድሞ መክፈሉም ተመልክቷል። በአጠቃላይ ኩባንያው 1 ቢሊዮን 765 ሚሊዮን 477 ሺ 726 ብር ከ27 ሳንቲም የልማት ባንክ እዳ ያለበት መሆኑ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
ይህ እዳ ተከፍሎ ሳያልቅ ኩባንያው ከወራት በፊት በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ምርቴን ከሰሜን ኢትዮጵያ ውጭ እንደልብ ተዘዋውሬ ለመሸጥና ከሌሎች በመሃል አገር ከተቋቋሙት መሰል የስሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ለመወዳደር ስለማያስችለኝ ስሚንቶን ወደ ማሀል አገር ለማመላለስ የሚረዱኝን 200 የጭነት መኪናዎችን ለመግዛት 721 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ብድር ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
መሰቦ ያቀረበው የብድር ጥያቄ እና የወሰደው ብድር ሙሉ በሙሉ ባንኩ ያወጣቸውን ህጎች የሚጥስ ሆኖ ተገኝቷል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከአምና ጀምሮ ለስሚንቶ ግንባታ ምንም አይነት ብድር እንዳይሰጥ ትእዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም፣ መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ ግን በልዩ ሁኔታ እንዲታይለት ተደርጓል። ባንኩ ለመሰቦ እስከዛሬ ያበደረው ብድር ለአንድ ኩባንያ ማበደር ከሚችለው የመጨረሻ ጣራ ላይ የደረሰ በመሆኑ፣ በባንኩ ህግ መሰረት መሰቦ ስሚንቶ ምንም አይነት ብድር ማግኘት ባይችልም፣ ኩባንያው ህግ ህግን በመተላለፍ የብድሩ ተጠቃሚ ሆኗል።
በባንኩ የውስጥ ህግ መሰረት ለሲሚንቶ እንዱስትሪዎች ባንኮች የሚያበድሩት ብድር ለብድር ካዘጋጁት መጠን 25 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት የተደነገገ ቢሆንም፣ መሰቦ ስሚንቶ ብድር በጠየቀበት ወቅት ባንኩ ያበደረው ብድር 30 በመቶ በመድረሱ፣ መሰቦ ስሚንቶ ብድር መውሰድ እንደማይስችለው በግልጽ ሰፍሮ ቢገኝም፣ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግን በልዩ ሁኔታ ብድር እንዲወስድ ተደርጓል።
ለግልገል ጊቤ 1፣ 2 እና 3 ፣ ለአባይ ግድብ ግንባታና በአገሪቱ ውስጥ መንግስት ለሚያካሂዳቸው ሌሎች ግንባታዎች በልዩ ሁኔታ ተፈቅዶለት በአብዛኛው ስሚንቶ በማቅረብ ላይ የሚገኘው መሰቦ ስሚንቶ፣ ለመኪና መግዣ የሚሆን ሃብት የለኝም በማለት ያቀረበው የብድር ጥያቄ ሌሎች ምክንያቶች እንደሚኖሩ የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የልማት ባንክ ቀዳሚ ተበዳሪ የህወሃቱ ኢፈርት ኩባንያ ነው።