መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ኢትዮጵያ እንድታከብር የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጠየቀ

ኢሳት (ጥቅምት 28 ፥ 2009)

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብርና በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የጣለውን ዕገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ሰኞ ጥሪን አቀረበ።

የህብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት ንኮሳንዛ ድላሚኒ ዙማ በሃገሪቱ ሰፍኖ ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ዕልባት ለመስጠት ሁለገብና ውጤታማ የሆነ ምክክር መካሄድ እንዳለበት ማሳሰባቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተግባራዊ አድርጎ የሚገኘው መንግስት የሃገሪቱ ዜጎች መረጃን የማግኘት እና የማህበራዊ ድረ-ገጾችን እንዲጠቀሙ ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲሉ ተሰናባቿ ሊቀመንበር ገልጸዋል።

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ህብረት፣ ባለፈው ወር ተመሳሳይ ማሳሰቢያን በማውጣት የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ ላለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ  መግለጫን ያወጣው የአፍሪካ ህብረት በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ተጥሎ ያለው እገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ ሲልም ጥሪውን አቅርቧል።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ተቋማት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ በመደረጉ ምክንያት ስራቸው መስተጓጎሉን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ይሁንና መንግስት በሃገሪቱ መረጋጋት እስኪሰፍን ድረስ አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደሚዘልቅ ምላሽን የሰጠ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግስት በአገልግሎቱ መቋረጥ ቅሬታውን እያቀረበ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ በታሰበው አመታዊው የአፍሪካ ህበረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ስጋትን እንዳሳደረም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ለኢሳት መገለጻቸው ይታወሳል።

በሃገሪቱ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናና ብዙሃን መግለጫን የሰጡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳንዛ ድለሚኒ ዙማ በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን እልባት ለመስጠት ምክክር ማካሄዱ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አክለው አሳስበዋል።