ጥር ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ ለአንዳንድ አንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የወጣው የደረጃ እድገት ማስታወቂያ በርካታ መምህራንን እንዳሳዘነ መምህራኑ ለኢሳት ገለጹ::
መምህራን እንዳሉት ለደረጃ እድገቱ እንደዋነኛ መስፈርት ሆነው የተቀመጡት፦ “በልማት ቡድንና በ1 ለ5 አደረጃጀቶች የሚያምን” ፣ ” በቡድኖቹ በመሳተፍ ውጤት ያስመዘገበ” የሚሉ እና ሌሎች ተመሳሳይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ነጥቦች ናቸው። እነኚህ መስፈርቶች ለመምህራን የደረጃ እድገት መቀመጣቸው፤ገዥው መንግስት- የትምህርት ተቋማትን ነጻነት በመጋፋት፤ትምህርት ቤቶችን እንዴት የራሱ ካድሬዎች ማስተማሪያ እንዳደረጋቸው የሚያሳይ ነው ሲሉ መምህራኑ ተናግረዋል::
በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ1 ለ5 አደረጃጀት በተጨማሪ “ኮማንድ ፖስት” የሚባል መኖሩን የገለጹት መምህራኑ፤ በዚህ አደረጃጀት ውስጥ የየትምህርት ክፍሎች የበላይ ተጠሪዎች እንዲታቀፉ ከተደረገ በሁዋአ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኘው የኢህአዴግ ሴል እንዲካተትበት ይደረጋል ብለዋል:: ይህም ገዥው ፓርቲ እያንዳንዱን የመምህራንና የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ፤ የፖለቲካ አቋምና ለኢህአዴግ ያላቸውን አመለካከት የሚሰለልበት ሌላው አደረጃጀት መሆኑን መምህራኑ ያስረዳሉ::
ተማሪዎቻቸውን በ1 ለ5 የማደራቸት ግዴታም እንደተጣለባቸው የሚገልጹት መምህራኑ ፤ በመምህራን የስራ አፈጻጸም ግምገማ በአብዛኛው ከቀለም ትምህርት አሰጣጥ ብቃት ይልቅ እንዲህ አይነት ጉዳዮች ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣቸው በሃዘን ገልጸዋል:: በደረጃ እድገቱ ከተጠየቁት መስፈርቶች ውስጥ ሌላው የተለያዩ ስልጣናዎችን የወሰደ እንደሚል የጠቀሱት መምህራኑ፤ ለትምህርት ቤቶች የሚመጡ ስልጠናዎች አብዛኞቹ የኢህአዴግ የራሱ የፖለቲካ ስልጠናዎች ከመሆናቸው አኳያ በስልጠናው ላይ የሚሳተፉት የፓርቲው አባላት አንደሆኑ ተናግረዋል። ይህ በደረጃ እድገቱ ውስጥ እንደአንድ መስፈርት እንዲቀመጥ የተደረገውም፤ የትምህርቱ ብቃት እያላቸው የፓርቲ አባላት ያልሆኑትን ለማግለል እንደሆነ መምህራኑ ይናገራሉ።
በአሰሩሩ ተስፋ የቆረጡ በርካታ መምህራን ስራቸውን እየለቀቁ ወደሌሎች ሙያዎች ውስጥ ለመግባት መገደዳቸውን የገለጹት መምህራኑ፤ አጠቃላይ የሚታየው ሁኔታ ሃገሪቷን መቼም ልትወጣው ወደማትችለው ውስብስብ ችግር ውስጥ እየከተታት እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል።