መለስ ዜናዊ ኦሮሞን አንደ ህዝብ ጠባብ ነው የሚል ሰነድ አዘጋጅተው እንደነበር አቶ ጁነዲን ሳዶ ገለጹ

ኢሳት (ጥቅምት 2 ፥ 2009)

የቀድሞ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ኦሮሞን አንደ ህዝብ ጠባብ ነው የሚል ሰነድ አዘጋጅተው እንደነበር አቶ ጁነዲን ሳዶ ገለጹ። በሁኔታው የተቆጩ በዝቅተኛ ዕርከን ላይ የሚገኙ የኦህዴድ ካድሬዎች ሰነዱ እንዲቃጠል መጠየቃቸውንም አስታውሰዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ከተዛወረ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ የተደረገው ቅንጅት አዲስ አበባ ላይ በማሸነፉ እንደሆነም ተመልክቷል።

የምርጫ 97 ማግስት ለኢህአዴግ ሰዎች እጅግ አስጨናቂ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጁነዲን ሳዶ፣ ዕርሳቸውና አቶ አባዱላ በምርጫ ክልላቸው ኢተያ ላይ በትክክል መሽነፋቸውን አምነዋል።

ኦሮሚያ ክልልን 4 አመታት ያህል በፕሬዚደንትነት ያገለገሉትና በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚንስትርነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ጁነዲን ይህንን የገለጹት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ሲሆን፣ በስርዓቱ ውስጥ የነበረውንና አሁንም እየቀጠለ ያሉት የህወሃትና የትግራይ የበላይነት በየአጋጣሚው ተቃውሞ ሲቀርብበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

በተለይም በህወሃት ክፍፍል ማግስት በጠ/ሚ/ሩ ጽ/ቤት ባደረጉት ስብሰባ በዚህ ረገድ ጠንካራ ተቃውሞ እንደቀረበባቸው አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ በነጻነት የሚናገሩበትና ተቃውሞ የሚያቀርቡበት መድረክ እንዳልነበርም አብራርተዋል።

የህወሃት ንብረት የሆነው ኤፈርት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እየወሰደ ሲፋፋ፣ ሌሎች ዲንሾን የመሳሰሉ የኦህዴድ ኩባንያዎች ስለመጫጨታቸው ለአቶ መለስ ጥያቄ መነሳትንም ያስታወሱት አቶ ጁነዲ ሳዶ፣ አቶ መለስ ለዚህ የሰጧቸው ምላሽ ኤፈርት የተቋቋመው ጆንያ ሽጦ ነው የሚል እንደነበር ገልጸዋል።

ለድርቅ ተጎጂዎች የመጣውን እህል ካደልን በኋላ ጆንያውን ሸጥን፣ በዚያም ኤፈርትን አቋቋምን ማለታቸው ተመልክቷል።

አቶ ጁነዲን ሳዶ በስልጣን ዘመናቸው በፌዴራል መንግስትና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለፉበትን ሁኔታ በተመለከተ ከኢሳት ጋር ያደረጉትን ሰፊ ቃለምልልስ ከነገ ጀምሮ በተከታታይ እናቀርባለን።