ሕዝባዊ እንቢተኝነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ማሽቆልቆሉ ተዘገበ

የካቲት ፰ ( ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመት (Foreign direct investment) በአንድ አምስተኛ ቅናሽ ማሳየቱ ብሉበርግ ዘግቧል። ሕዝባዊ አመጹን ተከትሎ ከባህር ማዶ የሚመጡ ባለሃብቶች መዋእለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሳተፍ ፍላጎታቸው ተቀዛቅዟል። በውጭ ባለሃብቶች ንብረት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ለኢንቨስተሮች ፍሰት ማሽቆልቆል በምክንያትነት ተጠቅሷል። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት የገባ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ግን አሃዙ ወደ 1.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መውረዱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋን በመጥቀስ ጋዜጣው ዘግቧል።
ንብረትነቱ የናይጀሪያዊው ባለሃብት የሆነው ዳንጎቴ የስሚንቶ ፋብሪካ እና የፍራፍሬ ማቀናበሪያን ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ባለሃብቶች ኩባንያዎች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል።
በአመጹ ጥቃት ለደረሰባቸው ለሃያ የአገር ባለሃብቶች እና ለሁለት የውጭ አገር ባለሃብቶች የታክስ እፎይታ ጊዜን ጨምሮ 100 ሚሊዮን ብር ወይም 4.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የካሳ ክፍያ ሰጥቷል።