ሕዝቡ የጀመረውን እምቢተኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2010)የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመረውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አለምአቀፍ የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረ ሃይል ጥሪ አቀረበ።

በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የጀመሩትን የዲፕሎማሲ እና የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ትግሉን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቋል።

አለም አቀፉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረሃይል ባወጣው መግለጫ እንዳለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተስፋና በስጋት ጊዜ ላይ ይገኛል።

በኢሕአዴግ ውስጥ የለውጥ አቀንቃኝነት ዝንባሌ ያላቸው ፖለቲከኞች ወደ ፊት አመራርነት መምጣታቸው እንደ ተስፋ ይታያል ነው ያለው።

ይህም ሆኖ ግን ሕወሃት ባዋቀረው የአገዛዝ ሰንሰለት ውስጥ ሆነው የሚያደርጉት ትግል ከጥገናዊ ለውጥ ያለፈ እንደማይሆን ገብረሃይሉ ገልጿል።

እናም ይህ ለውጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ባሟላ መልኩ መሰረታዊ መፍትሄ ስለማያመጣ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መመረጥ አዎንታዊ ቢሆንም የህወሃት አገዛዝ ሰራዊቱን፣የስለላ መዋቅሩን፣ኢኮኖሚውንና ቢሮክራሲውን ተቆጣጥሮ ስለሚገኝ ፋይዳ የለውምም ብሏል መግለጫው።

እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመረውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አለምአቀፍ የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረሃይል ጥሪ አቅርቧል።

ግብረሃይሉ የሕወሃት አገዛዝ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

በዚሁም መሰረት ግብረሃይሉ የጀመረውን የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ዘመቻ ላልተወሰነ ጊዜ በማራዘም እንቅስቃሴውን በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚገፋበት አስታውቋል።